Google search engine

አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ /ኢትዮጵያ ቡና/   “ጥሩ ጥሩ ተጨዋቾች መጥተዋልና የቡናን  የውጤት ጥማት ልናስታግስለት ይገባል” “ለኢትዮጵያ ቡና ለመጫወት ያመራሁት ክለቡን ስለምወደው ብቻ ሳይሆን ውጤትንም ከመፈለግ ነው” “አባቴ እና እኔ  ወደምንደግፈው ኢትዮጵያ ቡና ስላመራው ደስታዬ እጥፍ ድርብ ሆኗል”

 

ሊግ፦ በክረምቱ የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት ለኢትዮጵያ ቡና ለመጫወት ወደ ክለቡ  አምርተሃል፤ ወደ ቡና ገብቶ መጫወት የበፊት እልምህ ነበር?

አብዱልሀፊዝ፦ አዎን፤ ከልጅነቴ ጀምሮ ነው ቡና ገብቶ መጫወትን እልሜ የነበረው፤ በዛ ላይ እንደ አባቴ  የክለቡም  ደጋፊ  ነበርኩና ፈጣሪ ይመስገን ያን ለማሳካት የአዲሱን የውድድር ዘመን መጀመር እየተጣባበቅኩ ነው የምገኘው።

ሊግ፦ ወደ ቡድኑ ለመፈረም ስታመራ የነበረው አቀባበል ምን ይመስላል?

አብዱልሀፊዝ፦ በጥሩ ሁኔታ ነው እኔን የተቀበሉኝ፤ መጀመሪያ መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞንና አቶ ገዛኸኝን ነበር አግኝቼም ያወራዋቸው፤ ከእዛም በኋላ ወደ ቡድኑ ፅህፈት ቤት ሳመራ የቡድኑ የህዝብ ግንኙነት አላፊ የሆነው ዩሃንስ እድሉ /ጆኒም/ ነው በጥሩ ሁኔታ ተቀብሎኝና ውስጥ ካሉት ሰዎች ጋርም አስተዋውቆኝ ቀናቱን ያሳለፍኩት።

ሊግ፦ ወደ ኢትዮጵያ ቡና ከማምራትህ በፊት ወደ  እግር ኳሱ ዓለም የመጣህበት መንገድ ምን ይመስላል?

አብዱልሀፊዝ፦ እንደ ሌሎች ተጨዋቾች እኔ ብቻ ስለፈልግኩ አልነበረም ወደ ኳስ ተጨዋችነቱ የመጣሁት፤ የአባቴ ተፅህኖም ከፍ ያለ ነበር፤ ያኔ የስምንት ዓመት ልጅ እያለው ነበር አንተ ጥሩ ተጨዋች መሆን አለብህ ብሎኝ በማበረታታት እና ወደ ስታዲየም ይዞኝ በመሄድም ጨዋታዎችን እንድከታተል በማድረግ የኳሱ ፍቅር በደንብ እንዲያድርብኝ ያደረገው እና ዛሬም ላይ እዚህ ደረጃ ላይ እንድደርስ ያስቻለኝ፤ በእዚህ አጋጣሚ ወላጅ አባቴን ለእዚህ ስላበቃኝ በጣም ላመሰግነው እፈልጋለው

ሊግ፦ በልጅነት ዕድሜህ ስታዲየም  በመግባት የተከታተልከውን የመጀመሪያ ጨዋታን ታስታውሳለህ?

አብዱልሀፊዝ፦ የኢትዮጵያ ቡናን ጨዋታ ነው ያየሁት፤ ተጋጣሚውን ግን ልጅ ስለነበርኩ አላስታውስም፤ ያኔ እድሉ ደረጄ የክለቡ ካፒቴን ነበር።

ሊግ፦ በእግር ኳሱ ልጅ እያለህ ተምሳሌትህ /ሞዴልህ/ ተጨዋች ማን ነበር?

አብዱልሀፊዝ፦ ያኔ የሀገር ውስጥ ኳስን ብዙ አናይም ነበር፤ አባቴ ከነበረበት ስራ አኳያም ሜዳ ገብቶ ጨዋታ ለማየት ብዙም አይመቸኝም ነበር፤ በትምህርቴም ላይም ነበር ሳተኩር የነበረውና ከሀገር ውስጥ ተጨዋቾች ሞዴል ያደረግኩት ተጨዋች ማንም አልነበረም፤ ከባህርማዶ ተጨዋቾች ግን በጊዜው ወላጅ አባቴ በሲዲ የፕሪ ሲዝን ጨዋታዎችን ያመጣልኝ ስለነበር የአርሰናሉን ፋብሪጋዝ ነው በማየት እሱን ላደንቀው የቻልኩ፤ ፋበሪጋዝን በጣምም ነው የምወደው።

ሊግ፦ የእግር ኳስ ተጨዋች ባትሆን ኖሮ በምን ሙያ ላይ እናገኝህ ነበር?

አብዱልሀፊዝ፦ በእርግጠኝነት የምነግርህ በትምህርቴ ጥሩ ደረጃ ላይ እደርስ ነበር።

ሊግ፦ ከእናንተ ቤተሰብ ውስጥ  ሌላ ስፖርተኛ አለ?

አብዱልሀፊዝ፦ አሁን ላይ የለም፤ በፊት ግን ወንድሜ ኳስ ይሞክር ነበር፤ በኋላ ላይ ደግሞ በክፍለ ከተማ ደረጃ ለየካ ባስኬት ቦል ይጫወት ነበር፤ በወቅቱ ጥሩም ተጨዋች ነበር።

ሊግ፦ ውልደትህ እና እድገትህ የት ነው?

አብዱልሀፊዝ፦ ካሳንቺስ እንደራሴ በሚባለው አካባቢ ነው የተወለድኩት፤ ያደግኩት ደግሞ አቧሬ አካባቢ ነው።

ሊግ፦ ከቤተሰባችሁ ቀልደኛው ማን ነው?

አብዱልሀፊዝ፦ እናቴ ናት፤ እሷ አይናፈር ብትሆንም ከምታውቀው ሰው ጋርና ከእኛ ጋር ስትሆን ጥሩ ትቀልዳለች።

ሊግ፦ የእግር ኳስ ጅማሬህ ላይ ኳስ አትጫወት ተብለህ ተፅህኖ ተደርግብካል?

አብዱልሀፊዝ፦ በፍፁም፤ ወላጅ አባቴ እንደውም አንተ ጠንካራ ሁን እንጂ ሁለቱንም ማስኬድ ይቻላልም ይለኝ ነበርና በእዛ መልኩ ነው ኳሱን ፖዘቲቭ በሆነ መልኩ ተጫውቼው እዚህ ደረጃ ላይ ልደርስ የቻልኩት።

ሊግ፦ በእግር  ኳሱ እዚህ ደረጃ ላይ ደርሰሃል፤ የእልምህን ነው ያሳካከው?

አብዱልሀፊዝ፦ አዎን፤ የአባቴ ድጋፍም ነው ለእዚህ ደረጃ ያበቃኝ፤ ያለ እሱ ግን እዚህ መድረስ አይታሰብም ነበር።

ሊግ፦ የእግር ኳስ ጅማሬህ እና አሁን የደረስክበት ደረጃ ምን ይመስላል?

አብዱልሀፊዝ፦ የኳስ ጅማሬዬ ከሰፈር የሚነሳ ነበር፤ በአባሬ 28 ሜዳ ላይና በቤለር ሜዳም ነበር ስጫወት የነበረው፤ ያኔ  በአካባቢያችን ብዙ አሰልጣኞችም ነበሩና  እኔን ለማግኘት አባቴን ያነጋግሩት ነበር፤ በወቅቱ ግን አባቴ ለእነሱ ፕሮጀክት እኔን ለመስጠት ፈቃደኛ ፈቃደኛ አልነበረም፤ ይሄ ሊሆን የቻለውም ከትምህርት ጋር የልምምድ ሰዓቱ የሚመች ስላልነበር ነው፤ ኳስ የምጫወት ከሆነ የግድ ትምህርቱን መተው ነበረብኝና በፕሮጀክት ደረጃ ሳልጫወት ቀረው፤ በኋላ ላይ ግን እድሜዬ 14 እና 15 በደረሰበት ሰዓት የቤለር ሜዳ አሰልጣኝ የነበረው ኤልያስ ኢብራሂም ወደ አባቴ በመሄድ  ጊዜው  እየሄደበት ነው፤ አሁን ኳሱን ብታስጀምረው ጥሩ ነው ብሎት  ለአንድ ዓመት ለራህይ የፕሮጀክት ቡድን ከዛ በኋላም በቶማስ ለሚሰለጥነው ለአዲስ አበባ ምርጥ ተመረጥኩና ተጫወትኩ፤ በኋላም ላይ ወደ ደደቢት ቡድን ውስጥ በመግባት ከወጣት ቡድኑ አንስቶ የአምስት ዓመታት ቆይታን አደርጌ ለመጫወት ቻልኩኝ።

ሊግ፦ በእግር ኳሱ ትልቅ ደረጃ ላይ የመድረስ ራዕዩ ነበረህ?

አብዱልሀፊዝ፦ አዎ፤ እንደውም አባቴ እንዳሰበው አልሆነለትም፤ መሀል ላይ ጉዳትን ጨምሮ ብዙ ቻሌንጆች ነበሩ፤ ዘግይቻለው ብዬም አስባለው።

ሊግ፦ በፕሪምየር ሊግ ደረጃ መጀመሪያ ለማን ክለብ ተጫወትክ፤ የነበረህ የቡድኑ ቆይታስ ምን ይመስላል?

አብዱልሀፊዝ፦ የተጫወትኩት ለሰበታ ከተማ ነው፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት የቡድኑ ቆይታዬም ጥሩ ጊዜን ለማሳለፍ ችያለሁ፤ ይሄ ሊሆን የቻለውም የቡድናችን አሰልጣኝ የነበረው አብርሃም መብራቱ ጥሩ ነፃነትን ይሰጠኝ ስለነበር በእዛም ነው የተሳካ የሚባል ጊዜን ለማሳለፍ የቻልኩት።

ሊግ፦ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ አምና ጥሩ ውጤት አስመዝግቦ የነበረው ቡድናችሁ ዘንድሮ ከሊጉ ወርዷል፤ ሲወርድ በጣም አዘንክ?

አብዱልሀፊዝ፦ አዎን፤ አምና ጥሩ ነበርን፤ ሊጉን አምስተኛ ሆነንም ነበር ያጠናቀቅነው፤ በእዚህ ዓመት ላይ ግን ጥሩ አቅሙ ኖሮን ስንወርድ በጣም ነበር ያዘንኩት፤ ምክንያቱም እንዲህ ያለ ታሪክ በኳስ ህይወቴ እንዲያጋጥመኝ አልፈልግምም ነበር።

ሊግ፦ ሰበታ ከተማ ከሊጉ መውረድ ነበረበት ወይንስ አልነበረበትም?

አብዱልሀፊዝ፦ ጥሩ የተጨዋቾች ስብስብ ነበረን፤ ወደ ሜዳ  ከገባን በኋላም እንደምናደርገው ጥረት መውረድ ይገባናል ብዬ አላስብም፤ ኳስ ግን በዲስፕሊን ደረጃ በሜዳ ላይም ሆነ ከሜዳ ውጪ ከሌለ ጥሩ ውጤት ማምጣት የማይቻል ነውና በአሳዛኝ ሁኔታ ቡድናችን ሊወርድ ችሏል።

ሊግ፦ ለሰበታ ከተማ መውረድ በዋናኛነት የምታስቀምጠው ምክንያት ምንድን ነው?

አብዱልሀፊዝ፦ ከሜዳ ውጪ ዲስፕሊን አልነበርንም፤ ይህም ማለት ከደመወዝ ክፍያ ጋር የተያያዘውን ለማለት ነው፤ አስተዳደራዊ ችግሮችም ናቸው  ዋጋ ያስከፈለን።

ሊግ፦ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ተሳትፎ ሰበታ ከተማን እንደ አንድ ቡድን እንዴት ተመለከትከው?

አብዱልሀፊዝ፦ ለብዙ ቡድኖች ፈታኝ ሆነን ነበር፤ በኋላ ላይ ግን የሚገቡትን ኳሶች ስትመለከት፤ የሚሳቱ ኳሶችን ስታይ ከጀርባው ሌላ ነገርም እንዳለም ያስታውቃልና መውረድ ያልነበረበት ቡድን ነው የወረደው።

ሊግ፦ በሰበታ ከተማ ያለፉት ሁለት ዓመታት ቆይታህ ደስተኛ ነበርክ?

አብዱልሀፊዝ፦ አዎን፤ በግሌ ደስተኛ ነበርኩ፤ ለእዛም አላምዲሊላሂ እላለው።

ሊግ፦ የእግር ኳስን መጫወት ስትጀምር በአሁኑ የመጫወቻ ቦታ ነው?

አብዱልሀፊዝ፦ አልነበረም፤ በፊት ላይ የክንፍ አጥቂ ነበርኩ፤ በጣምም ፈጣንና ድሪብለርም ተጨዋች ነበርኩ፤ በኋላ ላይ ግን የልጅነቴ አሰልጣኝ ኤልያስ ኢብራሂም ነው ወደ መሀል ተጨዋችነቱ አምጥቶኝ እስካሁን በእዛ ቦታ ላይ እንድጫወት ያስቻለኝ።

ሊግ፦ በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመንህ በአንተ ስም የተመዘገቡ ጎሎችን ታስታውሳለህ?

አብዱልሀፊዝ፦ ደደቢት በነበርኩበት ሰዓት ለወጣት ቡድኑ ስጫወት ጎሎችን በተደጋጋሚ አስቆጥር ነበር፤ በፕሮጀክት ደረጃ ደግሞ በ14 ጨዋታዎች 8 ግብ ማስቆጠሬን አስታውሳለው፤ ሌላው ደግሞ አልፎ አልፎ ያገባሁበት ጊዜ ነበር።

ሊግ፦ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታህ ምርጡ ጨዋታችን ብለህ የምትጠቅሰው የትኛውን ግጥሚያ ነው?

አብዱልሀፊዝ፦ ከጅማ ጋር ያደረግነውን የካቻምና ጨዋታ ነው በዋናነት የምጠቅሰው፤ ከ600 በላይ ቅብብሎሽም ነበር ያደረግነው፤ ይሄ ጨዋታ ለእኔ የመጀመሪያዬ የሊጉም ጨዋታዬ ነበር፤ ሌላ የምጠቅሰው ደግሞ በእዛው ዓመት ላይ ከፋሲል ከነማ ጋር ያደረግነውን ነው።

ሊግ፦ በጣም የተከፋክበት እና ያዘንክበት ጨዋታስ?

አብዱልሀፊዝ፦ የዘንድሮውን ከአዳማ ከተማ ጋር የተጫውትነውን ነው የምጠቅሰው፤ ይሄን ጌም ያደረግነው ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎችን አሸንፈን ስለነበርና ይሄንንም ብናሸንፍ ያለመውረድ ተስፋው ይኖረን ነበር። ያም ሆኖ ግን ድካም ስለነበረብን እና ጥሩ ስላልተንቀሳቀስን ውጤቱ ሊሳካልን አልቻለም። ሊግ፦ ሰበታም ወረደ አንተም ወደ ኢትዮጵያ ቡና አመራህ፤ ሌሎች ጥያቄዎች ያቀረቡልህ ቡድኖች ነበሩ ?

አብዱልሀፊዝ፦ አዎን፤ በኤጀንቴ በኩል ጥያቄ ያቀረቡልኝ ቡድኖች ነበሩ፤ እኔንም በቀጥታ ያገኙኝ ነበሩ፤ ሆኖም ግን እኔም ሆንኩ አባቴ የቡና ደጋፊ ስለሆንን እና ለቡና መጫወትንም ስለፈለግኩ ወደ ክለቡ አመራሁኝ።

ሊግ፦ ለኢትዮጵያ ቡና ምን አይነት ግልጋሎትን ትሰጣለህ?

አብዱልሀፊዝ፦ በቅድሚያ ለቡድኑ ለመጫወት ፊርማዬን ስላኖርኩ በጣም ነው ደስ ያለኝ፤ ሲቀጥል ወደዚህ ቡድን የመጣሁት ውጤትን ፈልጌም  ነው፤ ቀላል ሁኔታም አይጠብቀኝምና ራሴን ብቁ አድርጌ በመምጣት እና በየጨዋታዎቹ ላይም የአቅሜን ሳልሰስት በመጫወት ቡናን ውጤታማ ማድረግ እፈልጋለው።

ሊግ፦ ለኢትዮጵያ ቡና ፊርማህን ስታኖር የክለቡ አመራሮች ምን አሉ?

አብዱልሀፊዝ፦ ይሄ ቡድን ውጤት ይፈልጋል፤ ብዙ ለውጦችን ያደረጉትም ይሄን ስኬት ፍለጋ እንደሆነም በአግባቡ ለእኔም ሆነ ለሌላ ወደ ቡድኑ ለመጡት አዳዲስ ተጨዋቾች የተነገራቸው ነገር አለና እንዲህ ያሉ ለትልቅ ቡድን የመጫወት እድሉ ሲመጣ አንተም በጥሩ ሁኔታ የምትዘጋጅበት ሁኔታ አለና የእነሱ ንግግርን ተግባራዊ ማድረግ የግድ ነው።

ሊግ፦ ወደ ኢትዮጵያ ቡና የመጡትን ተጨዋቾች እንዴት ትገልፃቸዋለህ?

አብዱልሀፊዝ፦ እኔ በበኩሌ በመጡት ተጨዋቾች ደስተኛ ነኝ፤ ብዙዎቹን በዲ ኤስ ቲቪ ጨዋታዎቻቸውን ስላየውም ቡድኑን የሚመጥኑ ናቸው፤ ጥሩ አቅም ያላቸው ልጆችም ነው የመጡት፤ ምንአልባት በውህደት ደረጃ ትንሽ ጊዜ ሊወስድብን ይችል ይሆናል እንጂ እነዚህ  ተጨዋቾች ወደ ቡድኑ በመምጣታቸው ደስ ብሎኛል።

ሊግ፦ ወደ አዲሱ ቡድንህ መጥተሃል፤ ስለ ክለቡ የምታውቀው ታሪክ አለ?

አብዱልሀፊዝ፦ አዎን፤ በተለይ ደጋፊዎቹ በጣም ነው የሚያስገርሙት፤ ከለራቸውን ሳይለቁም ነው ቡድኑን በጥሩ ሁኔታ የሚያበረታቱት፤ አሸንፈው ብቻ ሳይሆን ተሸንፈው ሁሉ የሚደግፉ ናቸው፤ በጣምም ይለያሉ።

ሊግ፦ እንደ ኢትዮጵያ ቡና ባለ ክለብ ውስጥ ስትጫወት ውጤት ሲገኝ ደጋፊው ተጨዋቾችን ያመሰግናል፤ ውጤት ሲጠፋ ደግሞ ሊቃወምህ ይችላልና እነዚህን ነገሮች ለማስተናገድ ዝግጁ ነህ?

አብዱልሀፊዝ፦ አዎን፤ ውጤት ሲጠፋ ደጋፊ የመናደድ መብት አለው፤ ሊቃወምክም ይችላል፤ ይሄን ልትከለክለው አትችልም፤ ግን ቅዋሜው የአንተንና የቤተሰብህን ክብር በማይነካ ቢሆን ደስ ይላል፤ ከዛ በተቃራኒ ሆነው ከተቃወሙክ ግን እነዚህ ደጋፊዎች ጊዜያቸውን ገንዘባቸውን ለቡድኑ ሰጥተው የሚመጡ በመሆኑ ቅዋሜያቸውን እንደ ክፋት አላየውም፤ እንደውም በእዛ መልክ ሲቃወሙክ ራስህን አሻሽለህ እንድትመጣም ነው የሚያደርጉህ።

ሊግ፦ ኢትዮጵያ ቡና የ2003ቱን የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ሲያነሳ የምታስታውሰው ነገር አለ?

አብዱልሀፊዝ፦ ያን ጊዜ አካባቢ ነው ቡድኑን የደገፍኩት፤ ሆኖም ግን በጊዜው ኳስን በፕሮጀክት ደረጃ እጫወት ስለነበር ብዙ የማስታውሳቸው ነገሮች የሉም።

ሊግ፦ ወደ ኢትዮጵያ ቡና አምርተሃል፤ የክለቡን መዝሙር ትችላለህ?

አብዱልሀፊዝ፦ ትንሽ ትንሽ አዎን።

ሊግ፦ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን  መከታተል ከጀመርክበት ጊዜ አንስቶ ለአንተ ምርጥ ተጨዋቹ ማን ነው?

አብዱልሀፊዝ፦ ዳዊት እስጢፋኖስን እና መስሑድ መሐመድን ነው በጣም ያደነቅኳቸው፤ የሚያስገርም ችሎታ አላቸው፤ ሁለቱን መለየትም ከባድ ነው፤ አብሬያቸው ልጫወትም ችያለሁ፤ ከእዛ ውጪ ጥሩ ጊዜን ከእነሱ ጋር በማሳለፍም ትምህርት ያገኘሁበት ሁኔታም ነበር። መልካም ሰዎችም ናቸው።

ሊግ፦ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን እንዴት አገኘከው?

አብዱልሀፊዝ፦ በመጀመሪያ ደረጃ ሊጉ በዲ ኤስ ቲቪ በመታየቱ እኛን እድለኛ አድርጎናል፤ ውድድሩም በጣም ደስ ይላል፤ ፎርማቱም ሊጉን አሳምሮታል፤ ጥሩ ፉክክር ተደርጎበትም ነው ሊጉ የተጠናቀቀው፤ ለዋንጫም ላለመውረድም በእዚህ መልኩ ውድድሩ ተደርጎ ሲዘጋ ደግሞ ለስፖርት አፍቃሪው የሰጠው እርካታም የአማረ ነበርና ወደፊትም ከእዚህ የበለጠ ምርጥ ውድድር ይኖራል ብዬ እጠብቃለሁ።

ሊግ፦ ባሳለፍነው የውድድር ዘመን አቡበከር ናስር ጎልቶ ወጥቶ ነበር፤ ዘንድሮስ ለአንተ ምርጥ ተጨዋቹ ማን ነው?

አብዱልሀፊዝ፦ ራሱ አቡበከር ነው፤ ያልተሰለፈባቸው ጨዋታዎች ቢኖሩም ቡድኑ እንደ አምናው ጥሩ ባይሆንም እሱ ግን ምርጥ ጊዜን አሳልፏል።

ሊግ፦ የኢትዮጵያ ቡናው አቡበከር ናስር ወደ ደቡብ አፍሪካው ሰንዳውንስ ክለብ አምርቷል፤ በኢትዮጵያ ቡና ከእሱ ጋር የመጫወት ፍላጎቱ ነበረህ?

አብዱልሀፊዝ፦ በጣም እንጂ፤ እሱን ከበፊት ጀምሮ አውቀዋለሁ፤ እድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች በነበረው የብሔራዊ ቡድን ጊዜ ላይም አብረን ተመርጠን ነበር፤ ያኔ እኔ ባለመንኩበት የኤም አር አይ ምርመራ ነበር የወደቅኩት።

ሊግ፦ የክረምት ወራት በምን መልክ እያሳለፍክ ነው?

አብዱልሀፊዝ፦ አስቀድሞ እና በቶሎ ለአንድ ቡድን ማለትም በጣም ለምወደው ለኢትዮጵያ ቡና በመፈረሜ ነገሮችን እርግት ባለ መልኩ እንዳይ እያደረገኝ ነው፤ ዝግጅቴን  በተረጋጋ መንፈስ ለመስራትም ዝግጁ ነኝ፤ ከዓላ እርዳታ ጋርም በጥሩ መልኩ ለመጪው የውድድር ዘመንም እቀርባለው።

ሊግ፦ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአሜሪካን እየተካሄደ ነው፤ ሀገራችን ጥሩ ውጤት እያስመዘገበችም ነው፤ በእዚህ ዙሪያ የምትለው ነገር ካለ?

አብዱልሀፊዝ፦ እየተመዘገበ ያለው ውጤት በጣም አሪፍ ነው፤ የስራ ውጤት እንደሆነም ያስታውቃል፤ በብዙ ነገሩ ከምልመላ ጀምሮ ሚዛናዊ እና በትክክል ስለተሰራም  ነው ስኬቱ ሊገኝ የቻለውና ሁሉም ነገር በጣም ደስ ይላል።

ሊግ፦ የአንተ ባህሪህ እንዴት ይገለፃል?

አብዱልሀፊዝ፦ ዝምተኛ ነኝ፤ ከብዙ ሰው ጋር ቶሎ የመግባባት ልምዱ የለኝም።

ሊግ፦ የተለየ የአመጋገብ ልምድ አለ?

አብዱልሀፊዝ፦ የለኝም።

ሊግ፦ ወደ አንድ ቦታ መሄድ ፈልገህ ባለመጓዝህ የሚቆጭህ ስፍራ?

አብዱልሀፊዝ፦ ሀጂ /መካ መዲና/ ባለመሄዴ፤ ዓላ ካለ እደርስበታለው፤ ወደዛ ብሄድ በጣም ደስ ይለኛል።

ሊግ፦ ከተመለከትካቸው ቦታዎችስ የወደድከው?

አብዱልሀፊዝ፦ ወደ ነጃሺ ሄጃለው፤ ያ መስኪድ የተሰራበት መንገድ እና ስለታሪኩ የሰማሁበት ሁኔታም በአግራሞት እንድመለከተው ነው ያደረገኝ።

ሊግ፦ በፆም ወቅት ሳትመገብ እግር ኳስን የምትጫወትበት ጊዜ አለና አይከብድም?

አብዱልሀፊዝ፦ ብዙ ተጫውቻለው፤ ከብዶኝም አያውቅም፤ እንደውም በእዛ መልኩ ስጫወት የመንፈስ ጥንካሬንም አገኛለው፤ እንደውም ከሌላ ጊዜ በበለጠም ጥሩ አቅሜን አውጥቼም እጫወታለው።

ሊግ፦ ለኢትዮጵያ ቡና ስትፈርም ስልክ ደውሎ መጀመሪያ እንኳን ደስ አለህ ያለህ ሰው ማን ነው?

አብዱልሀፊዝ፦ አባቴ ነው ለኳሱ በጣም ቅርብ ስለሆነ መጀመሪያ ላይ እንኳን ደስ ያለህ ያለኝ፤ ከዛ በኋላም ብዙ ሰዎችም ሊሉኝ ችለዋል።

ሊግ፦ የወደፊት ግብህ እና እልምህ ምንድን ናቸው?

አብዱልሀፊዝ፦ ዓላ ካለህ ቅድሚያ ሊጉ ላይ ከአዲሱ ቡድኔ ጋር ጥሩ ጊዜን ማሳለፍ እፈልጋለው፤ ከዛ ከውጪ ሀገር የሚመጡ እድሎችን መጠቀም እና ለብሄራዊ ቡድንም ተመርጦ መጫወትን እፈልጋለው።

ሊግ፦ እናጠቃል….?

አብዱልሀፊዝ፦  በእግር ኳስ ተጨዋችነቴ ለዛሬ እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ የብዙ ሰዎች እጅ አለበት፤ በቅድሚያ አላምዲሊላ ዓላን ማመስገን እፈልጋለው፤ ሲቀጥል ቤተሰቦቼን በተለይም ደግሞ አባቴን ከእሱ በኋላ ደግሞ እኔን በመምከርም ሆነ በማሰልጠን እንደዚሁም ደግሞ የመጫወት እድሎችን በመስጠት ያሰለጠኑኝን አሰልጣኞች ኤልያስ ኢብራሂምን፣ መለስ ገብርን፣ ሰለሞንን፣ ዳንሄል ፀሀዬን፣ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱንና  ይታገሱ እንዳለን ላመሰግናቸው እፈልጋለው።

 

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this: