Google search engine

“ለኢትዮጵያ ቡና ውጤት ማምጣት ዋንኛው ሰው ካሳዬና ካሳዬ ብቻ ነው” ኤርትራዊው የኢትዮጵያ ቡና ተጨዋች ሮቤል ተክለሚካኤል

 

ኤርትራዊው የኢትዮጵያ ቡናው የመሀል ሜዳ ተጨዋች ሮቤል ተክለሚካሄል በዘንድሮው የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የውድድር ተሳትፎአቸው አምና ያጡትን ዋንጫ ለማግኘት እንደሚጫወቱ ከሊግ ስፖርት ጋዜጣ አዘጋጅ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ጋር ባደረገው ቆይታ አስተያየቱን ሰጥቷል፤ እግር ኳስን በተወለደበት ኤርትራ ውስጥ መጫወት ጀምሮ የኳስ ህይወቱን እስከ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋችነት ድረስ ማስቀጠል የቻለው ይኸው ተጨዋች ከሊግ ስፖርት ጋዜጣ ጋር ስለ ኳስ ህይወቱና ወደ ኢትዮጵያ ቡናም ከተዘዋወረ በኋላ ስላለው የክለቡ ቆይታ ጥያቄዎች ቀርቦለት ምላሽን ሰጥቷል፤ ተከታተሉት፡፡

ስለ ውልደቱና እድገቱ

“የተወለድኩት በኤርትራ አስመራ ከተማ ውስጥ በተለየ ስሙ ገጀረት በሚባለው አካባቢ ነው፤ የአስተዳደጌ ሁኔታ ደግሞ ከሕፃንነት ዕድሜዬ አንስቶ ኳስን እየተጫወትኩ በማሳለፍና ትምህርቴን በመማር ነው”፡፡

የእግር ኳስን መጫወት ሲጀምር ቤተሰቦቹ ጋር ስለነበረው ፍላጎት

“ያኔ በትምህርቴ ጥሩ ስለነበርኩና በአንድ ወቅትም ጉዳትን አስተናግጄ ስለነበር ኳስን እንድጫወት ፈፅሞ አይፈቀድልኝም ነበር፤ ያም ሆኖ ግን ጉዳቱ በደረሰብኝ ጊዜ ለቤተሰቦቼ ኳስን መጫወት በጣም ነው የምወደው ጉዳትም የሚያጋጥም ነው ብዬ ከነገርኳቸው በኋላ መልሶ መግባባት ላይ ስለደረስንና የኳስ ስሜቴንም እየተረዱኝ ስለመጡም መጫወቴን ቀጠልኩበት”፡፡

የልጅነት ዕድሜው ላይ ኳስን ሲጫወት ያደንቃቸው ስለነበሩት ተምሳሌቱ ተጨዋቾች

“የመጀመሪያ ተጠቃሹና ያደነቅኩት ተጨዋች የቀድሞ የኤርትራ ብሔራዊ ቡድን ካፒቴን የነበረውን አብርሃም ቴዎድሮስን ነው፤ የእሱ ዋና አድናቂው ነበርኩ፤ ሌሎቹ ያደነቅኳቸው ተጨዋቾች ደግሞ አንዱ ለኤርትራ ብሔራዊ ቡድን 14 ቁጥር አድርጎ ይጫወት የነበረውንኤርሞንን ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የአባቴ ወንድም /የአጎቴ/ ልጅ የሆነውን ሄኖክ መድሃኔን ነበር አድንቄያቸው ተምሳሌቴ ያደርግኳቸው፡፡ ከእነዚህ ተጨዋቾች ውስጥ በተለይ የአጎቴ ልጅ የሆነውን ሄኖክ በወቅቱ ለአስመራ ቢራና ለተስፋ ቡድንም ይጫወት ስለነበር የእሱን ትጥቅ እየያዝኩለት በመሄድና ሲጫወትም ስለተመለከትኩም ጭምር ነው ወደ ኳሱ እንድሳብም ግፊት ያደረገብኝ”፡፡

ወደ እግር ኳሱ ባታዘነብል ኖሮ በምን ሙያ ላይ እናገኝህ ነበር

“የእግር ኳስ ተጨዋች ባልሆን ኖሮ ልገኝ የምችልበት ሙያ በእዛን ጊዜ ኳሴን እየተጫወትኩ የአልጋና የሶፋ ስራዎችን ከአባቴ ጋር አብረን እንሰራ ስለነበር በእዛ ሙያ ውስጥ ነበር የምገኘው፤ የእዛን ሰዓት ላይ ሁለቱንም ማለትም ኳሱንም ስጫወት ስራዬንም ከእሱ ጋር ስሰራ የተመከተኝ አባቴም አንተ ልጅ ከሁለቱ አንዱን ነገር መርጠህ ስራ ሲለኝም የእኔ ዋናው ፍላጎቴ ኳስ መጫወቱ ነበርና ወደዛ ሙያ ላይ ተሰማራው”፡፡

ወደ እግር ኳሱ እንድታመራ ግፊት ያደረጉልህ አካላቶች ካሉ

“እኔ የተወለድኩበት አካባቢ ገጀረት ይባላልና በሰፈር ደረጃ ስጫወት ብዙ አድናቂዎች ስለነበሩኝ በተለይም ትላልቅ የሆኑት ልጆች ሮቤል ጎበዝ ተጨዋች ነው፤ ከእኛም ጋር ትጫወታለህ በሚል መጀመሪያ በረኛ ከዛም ተጨዋች አድርገውም እያስገቡኝ መጫወት ጀመርኩና ከእዚህ በኋላም ነው ወደ ክለብ ተጨዋችነት ለማምራት የቻልኩት”፡፡

በእግር ኳስ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለተጫወተበት ክለብና ስለተከፈለው ደመወዝ

“የመጀመሪያው ክለቤ “ገጀረት” ነው የሚባለው፤ ያኔ በኤርትራ አስመራ ከተማ ውስጥ በአንደኛ ዲቪዚዮን ደረጃም ነበር የምንጫወተው፤ በጊዜው ኳሱን ስጫወትም በዕድሜዬ በጣም ትንሽ ልጅም ነበርኩና የተከፈለኝ የመጀመሪያ ደመወዝ 1ሺ 500 ብር ነበር”፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ የተከፈለውን ወርኋዊ ደመወዝ ምን ላይ እንዳዋለው

“ላሳደጉኝ ቤተሰቦቼ ለእናትና አባቴ ነበር እኩል አከፋፍዬ የሰጠዋቸው፤ በኋላ ላይ እኔ ጋር ምንም ገንዘብ እንደሌለ የተረዳው አባቴ ከሰጠሁት ብር ውስጥ ግማሹን ለእኔ መልሶ ሰጥቶኝ ከጓደኞችህ ጋር ሻይ ቡና በልበት ብሎ እንድደሰት ያደረገኝን ጊዜ መቼም የማልረሳው ነው”፡፡

ወደ ቀይባህር ነው ቀጥለህ ያመራኸው

“አዎን፤ ቀይ ባህር በኤርትራ ውስጥ በጣም ትልቅ ከሚባሉት ክለቦች መካከል ስሙ የሚጠቀስ ነው፤ ከዚህ ቀደም ኤርትራ የኢትዮጵያ ግዛት በነበረች ጊዜም በኢትዮጵያ ሻምፒዮና ይወዳደርና ጠንካራ ተፎካካሪ እንደነበርም ለማወቅ ችያለውና እኔም ከገጀረት ክለብ በኋላ ቀጥዬ የተጫወትኩበት ክለብ ይኸው ነው”፡፡

ለቀይባህር ለመጫወት ወደ ቡድኑ ስታመራ የፊርማ ክፍያ ተሰጥቶክ እንደሆነም ሰማን…

“የእውነት ነው፤ 40 ሺ የፊርማ ክፍያና ወርሃዊ ደመወዜ ደግሞ 1ሺ 700 ብር ተከፍሎኝ ነው ወደ ቡድኑ ያመራሁት፤  በጊዜው ለገጀረት ክለብ በምጫወትበት ሰዓት በጣም በጥሩ ብቃት ላይ ነበር የምገኘው፤ ከእኛ ክለብ ደጋፊዎች በተጨማሪም የሌላ ክለብ ደጋፊዎችና አመራሮችም እኔን በማድነቅ እስከ ቤታችን ድረስ የሚመጡበት ወቅትም ነበርና በተለይ የሌላ ቡድን ደጋፊዎችና አመራሮች ወደ እኛ ክለብ መጥተህ ብትጫወት ደስ ይለናል ይሉኝ ነበር፤ አዲስ አበባ ለሚገኘው ታላቅ ወንድሜ ጎይቶምም እኛ ጋር ቢገባ ጥሩ ነው አግባባው ይሉትም ነበር፤ ያም ሆኖ ግን ወደ ቀይባህር ለመግባት ለእኔ ምክንያት የሆነኝ የገጀረት አሰልጣኝ የነበረው ተወልደ ነው፤ ከገባክ ቀይባህር ግባ ቡድኑ ትልቅ ነው ራስህንም በደንብ ታሳይበታለህ ስላለኝ ወደ እነሱ ጋር ለማምራት ቻልኩ”፡፡

በኤርትራ ክለቦች በነበረህ ቆይታህ ያመጣችሁት ውጤት እና ስለነበረህ ቆይታህ

“ለገጀረት ስጫወት አንዴ ለነፃነት  በዓል ተጫውተን ዋንጫ አግኝተን ነበር፤ ሊጉን ደግሞ ታዳጊዎችም ስለነበርን በሶስተኝነት አጠናቀናል፤ ለቀይባህር ስጫወት ደግሞ በቆየሁባቸው ሶስት ዓመታቶች ጊዜ ውስጥ ሶስት የሊጉንና ሶስት ደግሞ የተለያዩ ዋንጫዎችን በማንሳት ስኬትን ልንጎናፀፍ ችለናል፤ እኔም እንደ ግል በጣም ምርጥ ጊዜን ለማሳለፍም ችያለው”፡፡

በኤርትራ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ስለነበረው ቆይታ

“በጣም ጥሩ ጊዜን ነው ያሳለፍኩት፤ ቡድኑን በአምበልነትም እየመራሁት ነው፤ ከሁሉም በላይ ያስደሰተኝ ደግሞ ሀገሬን ወክዬ ለመጫወት በመቻሌ ነው”፡፡

ለኢትዮጵያ ቡና ለመጫወት ስለመጣበት መንገድ እና  አሁን ላይ ተሰልፎ ስለመጫወቱ

“ለኤርትራ ብሔራዊ ቡድን ከተጫወትኩ በኋላ ወደ ቡና በቅድሚያ ያመራሁት በሴካፋ ላይ በነበረኝ የውድድር ተሳትፎ ላይ ታይቼ ነው፤ ያኔ ሁለተኛም ወጥተን ነበር፤ ጥሩ ስለተጫወትኩና ኮከብ ተጨዋች ስለተባልኩም በካሳዬ አራጌ አማካኝነት ተፈለግኩ፤ በወቅቱ እኔን ከቡና ውጪ የቻይና፣ የፈረንሳይ፣ የስዊድን እና የታንዛኒያው ያንግ አፍሪካ ክለቦች ይፈልጉኝም ነበርና ቅድሚያን ለቡና ሰጥቼ ቡድኑን ተቀላቀልኩ፤ ወደ ቡና ካመራሁ በኋላ ግን የምትገባው ተሞክረህና ታይተህ ነው ስባል ተበሳጭቼ ነበር፤ የእኛ ፌዴሬሽንም ሮቤል እኮ ፕሮፌሽናል ተጨዋች ነው በዛ ላይ በሌሎች ቡድኖችም ተፈልጓል ለምንድን ነው የሚሞክረው በሚል ተከራክሮልኝም ነበር፤ እኔም በጊዜው ሁኔታው ቢያናድደኝም ተሞከርኩና ለቡድኑ ተያዝኩ፤ አሁንም ብያዝም የመጫወት እድሉ በቦታዬ ሳይሰጠኝ ሲቀርም ከፍቶኝ ነበር፤ አሰልጣኝ ካሳዬ በተከላካይ ስፍራ ተጫወት ብሎኝ ነበር፤ እኔ ግን መሀል ላይ ነው የምጫወተው ብዬ ስነግረው  የመሀል ተጨዋችነት እድሉን ለሌሎች ልጆች ስለሰጠና በእዛ ወቀቅት ላይም በኮቪድም የተያዝኩበት ጊዜ ስለነበርም የውድድር ዓመቱን  በተጠባባቂነት አሳለፍኩ ዘንድሮ ግን ይህን የመሰለፍ እድል ከሲቲ ካፑ ጨዋታ ጀምሮ በተለያዩ ግጥሚያዎች ላይ እያገኘው ስለሆነ ደስ ሊለኝ ችሏል”፡፡

ለኢትዮጵያ ቡና ለመጫወት በመቻሉ

“ኢትዮጵያ ቡና ጥሩ ቡድንና ኳስን ፖሰስ አድርጎ የሚጫወት ጠንካራ ቡድን ነው፤ ወደዚህ ክለብ መጥቼ በመጫወቴም የተለየ ስሜት እንዲሰማኝም አድርጎኛል”፡፡

ስለ አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ

“በጣም ጥሩ አሰልጣኝ ነው፤ የራሱ የሆነ የኳስ ፍልስፍና አለው፤ በዛ ላይ ሀላፊነትን ይወስድልሃል፤ ሌላው ደግሞ ስለ መሰለፍ መብትህ ደፍረህ ስጠይቀውም የሚሰጥህ ምላሽ  አለ፤ እንድታከብረው ያደርግሃል፤ ቡና አምና ላመጣው ውጤት ዋንኛው ተጠቃሹ ሰው እሱ ነው፤ ወደፊትም ቢሆን ለቡና ውጤት ወሳኙ እና የመጀመሪያው ተጠቃሹ ሰው እሱ እና እሱ ነው”፡፡

ኢትዮጵያ ቡናን ዘንድሮ እንዴት እንጠብቀው

“የሊጉ ጅማሬያችን የአማረ አልነበረም፤ አሁን ግን ለውጥ አለን፤ ወደ አምናው ወደታወቅንበት አሸናፊነት እየተመለስን ነው፤ ይህን አሸናፊነት እናስቀጥለዋለን፤ ዘንድሮም ዋንጫውን ለማንሳት እንጫወታለን”፡፡

በመጨረሻ

“በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመኔ አሁን ካለኝ ብቃት ከፍ ባለ ስፍራ ላይ መገኘት እፈልጋለው፤ በፕሮፌሽናል ደረጃም ትልቅ ክለብ ውስጥ ገብቶ መጫወቱም ምኞቴ ነው፤ ይህን ካልኩ በኳሱ እዚህ ደረጃ ላይ እንድደርስ ላደረገኝ ፈጣሪዬ፣ ቤተሰቦቼ፣ ጓደኞቼና ያሰለጠኑኝን ሁሉ አመሰግናለው”፡፡

 

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this: