በአለምሰገድ ሰይፉ
እውን አንተ ከዚህ ሃላፊነት እንድትነሳ የተደረገው ተጨዋቾች በፈፀሙት ደባ ይሆን? ስለው “እንጃ… እንደዛ
ይሆናል ብዬ አላስብም፡፡ ከሆነም በዚህ ስራ የተጠመዱ ተጨዋቾች ካሉ ራሳቸውን ይፈትሹ” ብሎ ቆዘመ፡፡
ስዩም ውስጡ ክፉኛ እንደተጎዳ ገፅታው ያሳብቃል፤ ሃዘኑን ተጋራሁት፡፡ ይህ ምርጥ የሆነ አጨዋወት የሚከተል
ቡድን ማነፅ የሚችለው ጎልማሳው አሰልጣኝ ከመከላከያ ጋር የነበረው እህል ውሃ አሁን አብቅቷል፡፡
“የእውነት ከመከላከያ ጋር መለያየቴ የእግር እሳት ሆኖብኛል” አለኝ፡፡ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የጋዜጣው
ማኔጂንግ ኤዲተር አለምሰገድ ሰይፉ ከአሰልጣኝ ስዩም ከበደ ጋር ጣፋጭ ቆይታ አድርጓል፡፡ ተከታተሉን፤
ከጋዜጣችን በተጨማሪ በwww.leaguesport.net የተለያዩ ትኩስ መረጃዎች ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ሊግ፡- ሁሌም ቢሆን ከሊግ ስፖርት ጋዜጣ ለሚቀርብልህ ጥያቄ ያለአንዳች ማመንታት ለምትሰጠን ምላሽ ላቅ
ያለ ምስጋናዬን በማቅረብ እጀምራለሁ
ስዩም፡- እናንተም ሁሌም ቢሆን ላለፉት 16 አመታት ፕሮፌሽናል የሆነ አሠራርን ስለምትከተሉ እኔም ለእናንተ
ቃለ-ምልልስ ስሰጥ ሁሌም በከፍተኛ ደስታ ነው፡፡
ሊግ፡- በአሁኑ ሰአት ያለህ ስሜት ምን እንደሚመስል ግለፅልኝ እስቲ?
ስዩም፡- እንደስሜት ካየኸው ብዙ የተዘበራረቁ ነገሮች አሉ፡፡ ምክንያቱም ከመከላከያ ጋር እንደአማረው
አጀማመራችን አዲሱን የውድድር አመት በድርብ ዋንጫ ከማንሳታችን አንፃር የዘንድሮው የሊግ ታርጌታችን
ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ባለው ደረጃ ውስጥ ማጠናቀቅ ነበር፡፡ ከዚህ መነሻነትም በክለቡ በኩል የተደረገው
ድጋፍ በእጅጉ ከፍተኛ ነበር፡፡ እኔም ያለውን የተመቻቸ ሁኔታ በማየት ለክለቡ የተሻለ ነገር ለማሳየት ባስብም
የጠበቅኩት ነገር ሁሉ መክኖ በዚህ ሁኔታ መለያየታችን የፈጠረብኝ ስሜት ከፍተኛ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ሊግ፡- ስሜትህ ክፉኛ ተጎድቷል ማለት ነው?
ስዩም፡- አዎ፤ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ቢሆንም ግን ያሳለፍኩት የስልጠና ዘመን እጅግ ከፍተኛ ስለሆነ
ተደራራቢ ደስታና ሃዘንን በየተራ ስላየኋቸው ይህም አንዱ አካል ነው ብዬ ከመውሰድ በተረፈ በሆነ ጉዳይ ላይ
ራሴን ዝም ብዬ የማጨናንቅበት ምክንያት የለም፡፡
ሊግ፡- ስንብቱን ጠብቀኸው ነበር?
ስዩም፡- ምን መሰለህ ያለው እውነታ አንድ ሁለት ጨዋታ ተሸንፈህም ቢሆን ቀጣዩን ማሸነፍ አለብህ፡፡
አሊያም አንድ አቻ ተለያይተህ በቀጣዩ ጌም ውጤት መቀየር ሳትችል ቀርተህ መደዳውን መሸነፍ አደጋ አለው፡፡
ምንም እንኳን የቦርዱ አባላት በእኔ ላይ ያላቸው እምነት ከፍተኛ ቢሆንም ይህ ክለብ ታላቅ ከመሆኑ አንፃር
ሁሉን ነገር በዝምታ ቢያልፉ እነርሱንም የሚያስጠይቃቸው ነገር አለ፡፡ የአንደኛውን ዙር ጨዋታ ዝርዝር
ብታየው 5 ጨዋታ አድርገን በአራቱ ተሸንፈን በአንዱ አቻ ነው የተለያየነው፡፡ እናም በዚህ ሁኔታ ስንብት ሊመጣ
እንደሚችል እጠብቃለሁ፡፡ ሂደቱ ትክክለኛ ጊዜ ባይሆንም ይህ ነገር እንደሚፈጠር ባልገምት ነው
የሚገርመው፡፡ ሆኖም በሂደት የውጤት ለውጥ ይመጣል ብዬ ተስፋ አድርጌ ነበር፡፡ ቡድናችንም በሜዳ ላይ
የሚያሳየው የጨዋታ ብልጫና የሚመዘገበው ውጤት ፈፅሞ ለንፅፅር የሚቀርብ አልነበረም፡፡ እንደዛም ሆኖ
ግን ያሰብኳቸው ነገሮች ከስኬት ጋር ስላልተጣጣሙ መጨረሻችን መለያየት ሆኗል፡፡
ሊግ፡- እንደውም መከላከያ ስዩምን ለማሰናበት ዘግይቷል የሚሉም አልታጡም ልክ ናቸው?
ስዩም፡- እውነት ነው፡፡ እንደእኛ ሃገር ባህል ከሆነ መከላከያ እኔን ለማሰናበት ዘግይቷል፡፡ ምክንያቱም በሌላ
ቦታ ቢሆን ሁለትና ሶስት ጨዋታ እንኳን አትጠበቅም፡፡ በሃገራችን አሰልጣኞች ላይ እየታየ ያለው እውነታ ይህ
ነው፡፡ ነገር ግን የመከላከያ ሃላፊዎች በምክንያት የሚያምኑ ናቸው፡፡ ስለዚህ በሚገባ ይገመግማሉ፤
ሪፖርቶችህንም ያያሉ፤ እዛ ክለብ ሁሌም ጥልቅ የሆነ ውይይት ከተደረገ በኋላ ነው ውሳኔ ላይ የሚደረሰው፡፡
ከዚህ አንፃር ካየኸው በተለይ እኔን ከመጠን በላይ አስታመውኛል ማለት ይቻላል፡፡
ሊግ፡- ይሄን የመሰለ ምርጥ ስብስብ ይዘህ ውጤት የጠመመብህ ምስጢሩ ምንድነው?
ስዩም፡- ከውጤት ጋር መጣላት የጀመርነው ከአዳማ ከነማ ጨዋታ ጀምሮ ነው፡፡ በዚህ ግጥሚያ በሁለት
ደቂቃ ልዩነት ውስጥ ሁለት ተጨዋቾች በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጡ፡፡ በዛ ቀውጢ ውጤት 5ለ0 ነው
የተሸነፍነው፡፡ በቀጣይ ጨዋታም በቅዱስ ጊዮርጊስ በሰፊ ውጤት ተሸነፍን፡፡ ከዚያ በኋላ የቡድኑ ስሜት ጥሩ
መሆን አልቻለም፡፡ ከዚህ በተረፈ የእኛ ትልቁ ድክመት የመከላከል ባህሪያችን ነው፡፡ ይህም ማለት ከበረኛም፣
ከተከላካይም አሊያም ከሌላ ሴክተር ሊሆን ይችላል እነዚህ ሁኔታዎች ደግሞ በእጅጉ ዋጋ አስከፍሎናል፡፡ ከዚህ
ባሻገር ደግሞ ቀድሞ የሚቆጠርብን ግብ የነበረንን ነገር እንድናጣ መሆኑ ይመስለኛል፡፡
ሊግ፡- ታድያ ችግሩ ይህ መሆኑን ካወቃችሁ በሂደት ማስተካከል አይቻልም ነበር?
ስዩም፡- ብዙ ሞክረናል፡፡ ለምሳሌ እንኳን ከክለቡ ሃላፊዎች ጋር ተነጋግረን አዲስ አበባ ላይ የምናደርጋቸውን
ጨዋታዎች ቪዲዮ እናስቀርፃለን፡፡ ያንን የተቀረፀ ቪዲዮ በማየት ከተጨዋቾች ጋር በእያንዳንዱ እንቅስቃሴ
ዙሪያ ሰፊና ግልፅ ውይይቶችን እናደርጋለን፤ ግን የተፈጠረ ለውጥ የለም፡፡
ሊግ፡- ተደጋግሞ እየተነገራቸው መለወጥ ካልቻሉ የተጨዋቾቹ የመቀበል አቅም አናሳ ነው ማለት ይቻላል?
ስዩም፡- ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ደጋግመህ አሳይተኸው ተመልሶ ወደዛ ጥፋት የሚገባ ከሆነ ፐርፌክሽን
የለም ማለት ነው፡፡ እንደአሰልጣኝ ማድረግ የምትችለው በወሬ ከመናገር በላይ ተጨባጭ እንዲሆን በምስል
ደግፈህ ማስተማር ነው፡፡ ለምሳሌ ባለፈው ስንሸነፍ የነበረውን ክፍተት ነቅሰን በማውጣት ሁሉን ነገር
በተደጋጋሚ ለማሳየት ሞክረናል፡፡ ሆኖም መለወጥ የቻለ ነገር የለም፡፡
ሊግ፡- አንተ ከዚህ ክለብ እንድትለቅ ለማድረግ የተወሰኑ ተጨዋቾች በግሩፕ ተደራጅተው ያሴሩ ነበር የሚባል
ነገር ሰምቻለሁ፤ እውነት ነው?
ስዩም፡- በዚህ ጉዳይ ላይ ዘልቄ ገብቼ የማውቀው ነገር ባይኖረኝም አንዳንድ ጊዜ በጨዋታ ፍልስፍና ላይ
ከተወሰኑ ተጨዋቾች ጋር ዲስከስ የምናደርገው ነገር አለ፡፡ አንዳንድ ተጨዋቾች አጥቂዎቻችን ፈጣኖች ስለሆኑ
በረጅም ኳስ እንድረስ የሚሉ አሉ፡፡ አንዳንዱ ደግሞ ኳስ ይዘን እየተጫወትን እንድረሰ የሚሉ አሉ፡፡ በዚህ
ምክንያት በቡድኑ ተጨዋቾች መካከል ልዩነት እንዳለ ሰምቻለሁ፡፡ ይሄ ልዩነት እንዳለ ሆኖ የእኔ ፍልስፍና ደግሞ
ምን ይመስላል የሚለውን በግልፅ ተናግሬ እኔ የምፈልገውን ነገር እንዲያደርጉና በዛው ላይ የራሳቸውን
አስተሳሰብ ጨምረው እንዲጫወቱ ለማስቻል ብዙ ጥረት አድርጌያለሁ፡፡ አንድ መታወቅ ያለበት እውነት ደግሞ
ዞሮ ዞሮ ተጨዋቾች መገዛት ያለባቸው ለአሰልጣኙ ነው፤ ከዚህ በተረፈ ከላይ ላነሳኸው ጥያቄ እኔን
ለማሰናበት በማሰብ ተጨዋቾች አድማ ያደርጋሉ ብዬ አላስብም፡፡ ከሆነም የዚህ አይነት ልምድ ያላቸው
ተጨዋቾች ካሉ ራሳቸውን ይጠይቁ፡፡ በተረፈ ተጨዋቾቹ አሁንም ክለቡን የማዳን ትልቅ ሃላፊነት አለባቸው፡፡
በተረፈ በነበረን ቆይታ እኔ ያልተመቸኋቸው ነገር ካለ በቀጣዩ ጊዜ በሚመዘገበው ውጤት የሚታይ ይሆናል፡፡
ሊግ፡- በዘንድሮው የውድድር ዘመን መከላከያ ከሊጉ ቢወርድ ስዩም የታሪክ ተወቃሽ ይሆናል?
ስዩም፡- ዞሮ ዞሮ ፋይናል ውጤቱ ነው የሚታየው፡፡ ምክንያቱም የግድ ከተጠያቂነት አትሸሽም፤ ነገር ግን ይህ
ቡድን ምን እንደሚመስል አሳይቻለሁ፡፡ አምናም ሊወርድ በነበረበት ሠአት ደርሼ ቡድኑ እንዲተርፍ
አድርጌያለሁ፡፡ ከዛ በኋላ በነበረው የዝግጅት ጊዜ ጥሩ አድርገን በመስራታችን የጥሎ ማለፉንና ሱፐር ካፑን
ዋንጫ ስናነሳ የነበረን አቋም ልዩ ስለነበር የስፖርት ቤተሰቡ “መከላከያ ዘንድሮ ዋንጫውን ያነሳል” የሚል
ሰፊ ግምት ያሳደረበት ነበር፡፡ ይህም ማለት ቡድኑ ጥሩ ነገር እንዳለው ማሳያ ነው፤ ከዚያ በኋላ ቡድኑ በዚህ
ደረጃ መፍረክረኩ አብሮ ሊመጣ የሚችል ብዙ ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ የኳስ ምስጢሩን ባታውቀው እንኳን
የሚደበቁብህ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ከዛ በተረፈ ተጠያቂነቴ እንዳለ መሆኑን አልዘነጋውም፡፡
ሊግ፡- አሁን የተመዘገበው ጥሩ ያልሆነ ውጤት የአንተን የአሰልጣኝነት ሲቪ አያጠለሸውም?
ስዩም፡- በእኔ አይደለም በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ አቅም ላይ የደረሱ አሠልጣኞች አሉ፤ ለምሳሌ ያህል
ሞውሪንሆን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይህ አሰልጣኝ በታላላቅ የአውሮፓ ውድድሮች ላይ ምርጥ ውጤት አስመዝግቦ
ሳለ ከማንቸስተር ዩናይትድ የተሰናበተበትን ሁኔታ ሁላችንም ጠንቅቀን እናውቃለን፤ እናም ወደ እኔ ጋር
ስትመጣ ተመሳሳይ ነው፡፡ በተረፈ እኔ 80 በመቶ በአሰልጣኝነት ህይወቴ ስኬታማ ነበርኩ ብዬ ነው
የማስበው፡፡
ሊግ፡- በመከላከያ በነበረህ የአሰልጣኝነት ህይወትህ ምን የተማርኩት ነገር አለ ትላለህ?
ስዩም፡- በጣም ምርጥ ጥያቄ ነው ያነሳህልኝ፡፡ እዚህ ላይ በጥሩ ሁኔታ ተማርኩ ብዬ የማስበው ለዘብተኛ
ሠው መሆኔ ዋጋ እንድከፍል አድርጎኛል፡፡ ለምሳሌ እኔ የመን ለ6 አመታት ያህል ስቆይ በስጦታ ሳይሆን ሰርቼ
ማሳየት በመቻሌ ነው፡፡ ያውም በባዕድ አገር፡፡ የመን ያሉት ወጣቶች ከልጅነት ጀምሮ አስተዳደጋቸው ቤተሰብ
ጭምር በመነጋገር ያምናሉ፡፡ ማንም ሰው የራሱን አስተያየት ይሠጣል፡፡ እዚህም ቅዱስ ጊዮርጊስን ሳሰለጥን
የዲክታተርነት ባህሪ የለኝም፡፡ ከብዙ ተጨዋቾች ጋር በታክቲካል ጉዳዮች እወያያለሁ፡፡ የራሴን ሃሳብ
እሠነዝራለሁ፤ የእነርሱንም አዳምጣለሁ፡፡ ችግር ካለበት ጋርም እነጋገራለሁ፡፡ ከዚህ በተረፈ ቅጣት ላይም ገፍቼ
የምሄድበት ነገር የለም፡፡ መከላከያም እያለሁ የማደርገው ይህንኑ ነው፤ አሁን መለስ ብዬ ሳየው ግን እኔ ያን
ያህል መለሳለሴና ለዘብተኛ መሆኔ እንደጎዳኝ ነው የገባኝ፡፡
ምክንያቱም የግዴታ የውሳኔ ሰው መሆን አለብህ፤ ለምሳሌ ከተጨዋቾች ጋር ስንነጋገር ዛሬ እኔ አንተን
የማሰልፍህ እዛኛው ተጨዋች ላይ ይሄን የመሰለ ችግር ስላየሁበት ነው፡፡ አንተ ይሄንን ክፍተት ቀርፈህ መሄድ
አለብህ ስለው ሄዶ ለዛኛው ተጨዋች “ስዩም አንተን እንደዚህ ብሎሃል፡፡ እኔን ነገ ሊያሠልፈኝ ነው” ካለው ይህ
ራሱን የቻለ ትልቅ በሽታ ነው፡፡ ይህን እውነታ እያየሁትና እየሰማሁት ያለ ነገር ነው፡፡
የእኔ አስተሳሰብ የነበረው ግን በየተጨዋቹ ላይ ሞቲቬት ለመፍጠርና ከዚሁም መነሻነት ሁሉም ጠንክረው
እንዲሰሩ በማሰብ ነበር፡፡ በአንፃሩ ግን እነርሱ አመለካከቱን ወደሌላ ነገር መንዝረው ባልታሠበ መስመር
መግባታቸው ላይ ቀጥተኛ የሆነ ውይይት ማድረጉ ጉዳት እንደነበረው ተምሬበታለው፡፡
ሊግ፡- ስለዚህ…?
ስዩም፡- ስለዚህማ አካሄዱ ስለገባኝ ተምሬበታለሁ፤ እለወጣለሁም፡፡
ሊግ፡- ከዚህ በኋላ ለዘብተኛው ስዩም ይናፍቅሃል እያልከኝ ነው?
ስዩም፡- (ሳቅ) እሱን ወደፊት የምናየው ይሆናል፡፡
ሊግ፡- ከወልዋሎ አዲግራት ጋር ለመጫወት ወደመቀሌ ለመጓዝ በተዘጋጃችሁበት ጊዜ ደውዬልህ “ክለቡ
እየተሸነፈ አመራሮቹ እኔን በዝምታ ማለፋቸውን ሳስበው በጭንቀት ማበዴ ነው” ብለኸኝ ነበር እስቲ የዛን
ጊዜ የነበረው ስሜት ምን ይመስል እንደነበር ግለፅልኝ?
ስዩም፡- ከድሬዳዋ ጋር አቻ ወጣን፡፡ በመቀጠል ከደደቢት ጋር ነው የተጫወትነው፡፡ ይህ ክለብ ደግሞ በሊጉ
የደረጃ ሰንጠረዥ ግርጌ ላይ ያለ ቡድን ከመሆኑ አንፃር እኔም ሆንኩ ተጨዋቾቼ ከዚህ ጨዋታ የምንጠብቀው
ሶስት ነጥብ ነው፡፡ ሆኖም ያንን ውጤት እንኳን አጥተን ሳለ የክለቡ አመራሮች ስሜታቸው ሳይነካ “አይዞህ
ውጤቱ ይለወጣል፤ ትዕግስት አድርግ” እያሉ ሲያበረታቱኝ ሳይ ላምን አልቻልኩም፤ በዚህን ወቅት ከመፅናናት
ይልቅ ስትረሱ ነው የበዛብኝ፤ ዛሬ በርካታ ክለቦች በሁለትና በሶስት ጨዋታ ውጤት አሰልጣኞቻቸውን
ሲያሰናብቱ እያየን ከመከላከያ ሃላፊዎች ይሄን የመሰለ ጠንካራ ድጋፍ ሲደረግ ሳይ ለእኔ ሌላ ተጨማሪ ጫና
ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ከዛም ነው አንተ በደወልክልኝ ጊዜ እንደዛ ያልኩህ፤ ከዛ በተረፈ ክለቦች ከመከላከያ
ብዙ ነገር ሊማሩ ይገባቸዋል፤ በጣም የሚገርምህ ነገር ባለፈው ጊዜ ከድሬዳዋ ጋር አቻ ነው የተለያየነው፡፡
ለአቻ ውጤት ደግሞ ኢንሴንቲቭ የለውም፡፡ ነገር ግን የክለቡ ሃላፊዎች እኛን ለማበረታታት በማሰብ ብቻ
እንዳሸነፈ ቡድን ኢንሴንቲቭ እንዲሰጠን አድርገዋል፡፡ ይሄን ሳስበው ከመከላከያ መልቀቄ የእግር እሳት ነው
የሆነብኝ፡፡
ሊግ፡- አሁን የሊጉ ውድድር እየተገባደደ ከመሆኑ አንፃር በቀሪው ጊዜ ለማረፍ አስበሃል፤ አሊያስ ሌሎች
ክለቦችን እየቃኘህ ነው?
ስዩም፡- በዚህ ሰአት ሌላ ክለብ መግባቱ ሪስክም ከመሆኑ ባሻገር ከሙያ ስነ-ምግባር አንፃርም ተገቢ
አይደለም፡፡ በመሆኑም ትንሽ ማረፍ እፈልጋለሁ፡፡ በተረፈ ምንም እንኳን ከክለቡ ብሠናበትም መከላከያን
በተቻለኝ አቅም ከውጪ ሆኜም ቢሆን ማገዝ እፈልጋለሁ፡፡ ለምሳሌ እንኳን ለዚህ ኢንተርቪው ቀጥረኸኝ
አንተ ጋር ከመምጣቴ በፊት ከክለቡ አመራሮች ጋር እያወራን ነበር፡፡ ምክንያቱም ይህ ክለብ ከሊጉ የመውረድ
አደጋ ቢተርፍ የእኔም ደስታ ስለሆነ በተቻለኝ አቅም ሁሉ መከላከያን ለማገዝ ዝግጁ ነኝ፡፡
ሊግ፡- አጋጣሚው ተፈጥሮ በአገራችን ካሉት ታላላቅ ክለቦች መካከል ከቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና
የአሰልጣኝነት ጥያቄ ቢቀርብልህ ምላሽህ ምን ሊሆን ይችላል?
ስዩም፡- አሁን እኔ በጥሩ ሁኔታ የበሠልኩበት ደረጃ ላይ ነው ያለሁት፡፡ ብዙ ልምዶችም አሉኝ፤ እናም ካለኝ
የተካበተ ልምድ አንፃር እነርሱንም ባሠለጥን ምንም አይነት ችግር የለብኝም፡፡
ሊግ፡- በአንድ ወቅት ከሚዲያ ጋር ውዝግብ ውስጥ የገባህበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር፤ ምክንያቱ ምንድነው?
ስዩም፡- እውነት ለመናገር ትክክለኛውንና ፕሮፌሽናል መንገዱን ተከትሎ ማንም ሰው ስለክለቤ ቢተችና
ቢዘግብ ከዛ ትችት ልትማርበት ትችላለህ፡፡ ነገር ግን ፐርሰናል አታክ ሲሆን ያስጠላል፤ ይህ ደግሞ በገሀድ
የማየውና በድግግሞሽ የምሠማው ነው፡፡ በቲቪም በሬድዮም እየመጡ የአንተን ትንሽ ነገር እየተፈለገ ስንጥቅ
እያወጡ የሚደረገው ትችት ማንንም አያስተምርም፡፡ አይጠቅምም፡፡ ምክንያቱም እነርሱ ሚዲያውን
እንደመሳሪያ ተጠቅመው ያንን ተናገሩና እኔን ለዘመናት በዚህ ስፖርት ላይ የሚያውቁኝ ማህበረሠብ ስምና
ዝናዬን ጥላሸት ይቀባዋል ማለት አይደለም፡፡ እናም ይህ ነገር ባይለመድና ማንኛውም ሚዲያ ፕሮፌሽናል በሆነ
አካሄድ ትችትና ሃሳቡን ቢሰነዝር ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ ረገድ ችግር ያለባቸው ጋዜጠኞች ስላሉ
እግዚአብሄር ይቅር ይበላቸው ነው የምለው፡፡
ሊግ፡- ለመሰናበቻ ምን ትላለህ?
ስዩም፡- ሁሉንም ነገር ስለዳሠስነው ከዚህ በዘለለ ብዙም የምለው ነገር የለም፡፡ ሆኖም በሃገሪቱ ውስጥ
ከፍተኛ የሆነ የስራ ጫና እያለባቸው የክለቡ አመራሮች የነበራቸው ተነሳሽነት የሚገርም ነበር፡፡ ለምሳሌ
ሌተናል ጄኔራል መሃመድ ጊዜያቸውን ሁሉ መስዋዕት እያደረጉ ይህ ታላቅ ክለብ የላቀ ደረጃ ላይ እንዲደርስ
ለማስቻል ብዙ ለፍተዋል፡፡ በተለይ መከላከያ በኢንተርናሽናል የውድድር ተሳትፎ ጥሩ እንዲጓዝ ለማስቻል
የሚቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል፡፡ የእነዚህ አይነት ሰዎች ለሃገሪቱ ስፖርት በእጅጉ አስፈላጊ በመሆናቸውም
ለእነርሱ ከፍተኛ የሆነ ከበሬታ አለኝ፡፡
በተረፈ የስፖርት ክለብ ሃላፊው ሌተናል ኮሎኔል ደረጄ፣ ኮ/ል ደሱና ብዙ ቅን ሰዎች ክለቡ ውስጥ አሉ፡፡ እናም
እነዚህ ለክለባቸው ሟች የሆኑ ግለሠቦች መከላከያ ከሊጉ ተርፎ የተሻለ ነገር ያዩ ዘንድ ልባዊ ምኞቴ ነው፡፡
በነበረኝ ቆይታም ድጋፋቸው ላልተለየኝ ሁሉ በልዑል እግዚአብሄር ስም ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡