Google search engine

“በእግር ኳስ ዘመኔ ምርጡ ጨዋታዬ ከቡና ጋር ያደረግኩት ነው፤ ከመስዑድና ከኤልያስ ጋር መጫወት ምኞቴ ነው” በሀይሉ ተሻገር /አኪራ/ ሀድያ ሆሳህና/

የሀድያ ሆሳህናው የአማካይ ስፍራ ተጨዋች በሀይሉ ተሻገር /አኪራ/ እግር ኳስን ለመብራት ሀይል ክለብ እና ለኢትዮጵያ ወጣት ቡድን ተጫውቶ ያሰለፈ ሲሆን፤ በጥሩ ተጨዋችነቱም ይታወቃል፤ ይህን ተጨዋች ስለ ህይወቱ ከእግር ኳስ ጋር በተገናኙ ጉዳዮች እና ስለ ኮሮና ቫይረስ አናግረነው የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቶናል፡፡
ስለ ኮቪድ 19 እና የእግር ኳሳችን ስለመቆሙ
“ኮቪድ 19 እንደ ሀገር ሳይሆን እንደ ዓለም ስለሆነ የመጣው ወረርሽኙን በተመለከተ ትንሽ ከባድና አስቸጋሪ የሆነ በሽታ ነው፤ የእግር ኳሱም በእዚህ ክፉ ቫይረስ ምክንያትም በመቋረጡ ምንም ነገርንም ማድረግ አትችልም፤ ስለዚህም ፈጣሪ እንደዚህ አይነቱን በሽታ ያጥፋልን፤ አገራችንንም ይጠብቅልን ነው የምለው”፡፡
አሁን ላይ ከእግር ኳስ ጨዋታ ርቆ ስለመቆየቱ
“ከእግር ኳስ መራቅ ኳስን በጣም ለሚወድ ሰው ከምነግርህ በላይ በጣም አስቸጋሪ እና ከባዱም ነገር ነው፤ እንደምናወራው ብቻም አይገለፅም፤ ኳስን መጫወት ለምደህ እንደዚሁም ደግሞ በኳሷ መዝናናት እና ሰዎችንም ማዝናናት ችለህ አሁን ላይ ያለ ኳስ እቤትህ ውስጥ ለብዙ ጊዜያት ቁጭ ስትልና ስትውል የማይቻልም ነው፤ ኳስን ቀን በቀን የሚጫወት ሰው አመጫወት ማለት ትንሽ የሚከብድም ነው፤ ኳሱ ለእኛ እንጀራችን ሆኖ ቀን በቀን ስለምንሰራውና ስለምናገኘውም ምግብም በለው፤ ኳስ አለመጫወትና ልምምድ አለመስራት ማለት ምግብ አለመብላት እንደማለትም አይነት ነውና ከኳሱ ርቆ መቆየቱ ትንሽ ከበድ ይላል”፡፡
የእግር ኳሱ ከቆመ በኋላ ያለውን ጊዜ በምን መልኩ እያሳለፈ እንደሆነ
“በኮቪድ 19 ምክንያት የእግር ኳሱ መቆሙ የምታደርገውን እንቅስቃሴ ሁሉ በተወሰነ መልኩ ስለሚገድብብህ በሽታውም በጣም አስከፊና ተላላፊም በመሆኑ ይሄ ቫይረስ የሚያመጣብህ ተፅህኖ አለና ይሄን ተፅህኖ ለማለፍ በምን መልኩ ነው ጊዜያቶቹን የማሳልፈው? እንዴትስ ነው የምወጣው? በሚል እቤት ውስጥ በማደርገው የስፖርት እንቅስቃሴ ነው ራሴንም ሆነ ቤተሰቦቼን በማይጎዳ መልኩ ወቅቱን እያሰለፍኩ የምገኘው፤ ከዛ ባሻገር ደግሞ ከቤት ብዙም ስለማልወጣም የጤና ጥበቃና መንግስት ያወጣቸውን ለምሳሌ እጅን በሳሙና መታጠብን፣ ሳኒታይዘር መጠቀምን፣ እንደዚሁም ደግሞ ተራርቆ መቀመጥንና መቆምን እንደዚሁም ደግሞ ሌሎችንም መመሪያዎች እያከበርኩኝና ራሴም እየተገበርኩትም ነው የምገኘው፤ ከቤት አለመውጣት ደግሞ አንተን ብቻ ሳይሆን ቤተሰብህን፣ ጓደኞችህን፣ ሀገርህንም በጣም ይጠቅማልና በእዚህ መልኩም ኃላፊነታችንን መወጣትም የተሻለም ነው ብዬ አስባለውና ጊዜዎቼን የማሳልፈውም በእዚሁ ሁኔታ ነው”፡፡
እስካሁን ስለጨረሰው የሳኒታይዘር ብዛት
“ሳቅ ካለ በኋላ ሁለት ትላልቅ ሙሉ ሳኒታይዘሮችን ጨርሻለሁ፤ ማክስ ራሱ በቁጥር ባላቃቸውም ብዙ ጨርሻለሁ”፡፡
በእግር ኳሱ መቆም ላይ በዋናነት የናፈቀህ
“በኮቪድ 19 ምክንያት የሊግ ውድድሩ በመቋረጡና ከቤትም ብዙ አትውጡ በመባሉ በዋናነት የናፈቀችኝ ብትኖር ወላጅ እናቴ ናት፡፡ የአሁን ሰዓት ላይ ከእሷም ጋር ተራርቀንም ነው እየኖርን ያለነው፤ በፊት ላይ ኳስ በምጫወት ሰአት እናቴን የማገኛት አጋጣሚዎች ነበርና እሷ ናፍቃኛለች፤ ሌላው የናፈቀኝ ነገር ቢኖር በአዲስ አበባ ስታድየም በእዛ ሁሉ የእግር ኳስ አፍቃሪ ፊት ኳስ መጫወትም ነው”፡፡
የስፖርት እንቅስቃሴዎችን ከመስራት ውጪ የእረፍት ጊዜውን የሚያሳልፍበት የተለየ ነገር
“ብዙውን ጊዜ የመንፈሳዊ ቻናሎችን በመከታተልና መፅሐፍ ቅዱስንም በማንበብ ነው ጊዜውን እያሳለፍኩ የምገኘው”፡፡
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር የዘንድሮ ውድድር በመቋረጡና በመሠረዙ እንደተጨዋችነቱ ምን እንደሚል
“የእግር ኳስ ጨዋታው መቋረጡ ተገቢ ነው ብዬ ነው የማስበው፤ ምክንያቱም የሰው ልጅ ሲኖር ነው ምንም ነገርን ማድረግ የሚቻለው፤ ከሌለ ምንም ነገር የለም፤ አይደለም ኳሱ አንተ ራሱ ካልኖርክ ምንም ነገርም አይኖርምና እንደጤና ጥበቃ ሚኒስትርና እንደ መንግስትም ከጤናና ህይወት የሚበልጥ ነገር ስለሌለ በኳሱ መቋረጥ ላይ የተወሰነውን ውሳኔ ትክክለኛም ነው ብዬ አስባለው፤ ፈጣሪም ይሄን በሽታ ያጥፋልንና በሚቀጥለው ዓመት ሊጉን መንግስትም ፌዴሬሽኑም ይጀምረዋል ብዬም ነው የማስበው”፡፡
የሊግ ውድድሩ ሲቋረጥ እንደ ሀድያ ሆሳዕና ክለብ ተጨዋችነትህ ከክለቡ ጋር ስለነበራችሁ የመጨረሻው ቀን ግንኙነት
“የሀድያ ሆሳዕና ክለብ ኮቪድ 19 ወደ ሃገራችን መግባትን ሲያውቁ ይህ ወረርሽኝ እንዲህ ባለና ኳሱን በሚያቋርጥ ደረጃ ላይ ይደርሳል ብለው ፈፅሞ አልጠበቁም አላሰቡምም ነበርና መንግስት ባወጣው መመሪያና ህግ መሰረት ኳሱ እንዲቋረጥ ሲደረግና ከእነሱም ጋር ባለው ሁኔታ ላይ ለመጨረሻ ጊዜ ስንነጋገር የነበረን ግንኙነት በሽታው ቶሎ ይገታል ብለው አስበው ነበርና እንደዉልላችዋለን ስንጠራችሁም ትመጣላችሁ በሚል ነበር የሊጉን ውድድር በመቀላቀል ወደ ጨዋታ እንደምንገባ አስበው የነበረውና ፈጣሪ ስላልፈቀደው ያ ሳይሆን ቀርቷል”፡፡
በኮቪድ 19 እኛ ሃገር ላይ ጥንቃቄ እየተደረገ ነው
“እኔ ሙሉ ለሙሉ ማለት እችላለው አሁንም ቢሆን ጥንቃቄው እየተደረገ አይደለም ብዬ ነው የማስበው፤ አልፎ አልፎ በምወጣበት ሰአት የማያቸው ነገሮች እንኳን በሽታ ያለ ሊመስል በሽታው ሌላ ነገር ማለትም ቫይረሱ ይታደላል በሚባል ደረጃ ነው ሰዉ እንቅስቃሴን እያደረገ የሚገኘው እና ይሄን እንቅስቃሴ በቸልተኝነት ባያዩትና ቢያንስ አንድ ሰው አንድ የሚወደው ሰው ከአጠገቡ አለና ለእሱ ሲል ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ህዝቡም ቸልተኝነቱን መተው አለበት፤ ምንም ነገርንም ችላ ባይልም ጥሩ ነው፡፡ አስፈላጊውን ጥንቃቄም ወስዶ እንደ ሳኒታይዘርና ማክስን በአግባቡም በመጠቀምና እጁን በሳሙና በመታጠብም መንግስትና ጤና ጥበቃ ያወጣውን መርሆች በአግባቡ ቢከተል መልካም ነው እላለው፤ ምክንያቱም አለማወቅ ላያድን ይችላል፤ አሁን ማወቅ ነው የሚያድነው፤ ስለዚህም ወደማወቅ መሄድ ይሻላልና ሰው ይህን የቫይረሱን በሽታ አደገኛነት ተገንዝቦና ለመንግስትም ተገዥ ሆኖ በጥንቃቄ ቢራመድና በህይወትና በጤናም ለመኖር ቢጥር ጥሩ ነው”፡፡
የእግር ኳስ ዘመኑ ላይ ምርጥ ጨዋታዬ ብሎ ስለሚያስበው
“በእግር ኳስ ጨዋታ ዘመኔ ጥሩ በመንቀሳቀስ ለእኔ በቀዳሚነት ስፍራ ላይ የማስቀምጠው ምርጥ የምለው ጨዋታዬ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በአበበ ቢቂላ ስቴድየም ያደረግነው እና ለናይጄሪዊው አጥቂ ፒተር አቀብዬው እሱ ባስቆጠረው ግብ 1-0 ያሸነፍንበትን ነው”፡፡
የጨዋታ ዘመኑ ላይ በየመጫወቻ ቦታው የእኔ ምርጦች ስለሚላቸው ተጨዋቾች
“ከግብ ጠባቂ ስጀምር የቅዱስ ጊዮርጊሱ ሮበርት ኦዶንካራን እመርጣለው፤ ከተከላካይ ደግሞ በረከት ተሰማን፤ በመሃል ሜዳ ላይ ደግሞ አዲስ ነጋሽን ነው እሱ በተለይ እንደፈለግኩ እንድንቀሳቀስ ከማድረጉ በተጨማሪ ጥሩም ተጨዋች ነውና አዲሴ ምርጫዬ ነው፤ ከአጥቂዎች ደግሞ ከናይጄሪያዊው አጥቂ ፒተር ጋር ጥሩ ቅንጅት ነበረንና እሱን ነው በቀዳሚነት የምመርጠው”፡፡
ሁሌም አብሬው ብጫወት ብለህ የምትመኘው ተጨዋችስ
“ከእነዚህ ተጨዋቾች ጋር እስከአሁን ድረስ አብሬያቸው ባልጫወትም ከአጠገባቸው ሆኜ ልጫወት የምፈልጋቸው ተጨዋቾች መስዑድ መሃመድ እና ኤልያስ ማሞ ናቸው፤ አንድ ቀን አብሮ መጫወቱም ይሳካልኛል ብዬም አስባለው”፡፡
ስለባለቤቱና ስለ ትዳር ህይወቱ
“ባለቤቴ አዲስ ተክሉ ትባላለች፤ የተክለሀይማኖትም ልጅ ናት፤ በጣምም ነው የምንዋደደው፤ ጥሩ የትዳር ህይወትንም እየመራን ነው”፡፡
በመጨረሻ…..
“በመጀመሪያ ለእዚህ አሁን ለምገኝበት ደረጃ እንድደርስ ለረዳኝ ፈጣሪዬ ከፍተኛ ምስጋናዬን አቀርባለው፤ በመቀጠል ደግሞ የልጅነት እድሜዬ ላይ አስኮ አካባቢ ለሚገኘው የፕሮጀክት ቡድናችን ኳስን ስጫወት እኔን ላሰለጠኑኝ አሰልጣኞችና ከዛ በኋላም በክለብ ደረጃ ላሰለጠኑኝ አሰልጣኞች እንደዚሁም ደግሞ በጣም ለምወዳት እናቴና ባለቤቴ፤ በምክርና በተለያዩ ነገሮችም ለደገፉኝ ሁሉ ምስጋናዬ ከፍ ያለ ነው፡፡ ይህን ካልኩ ፈጣሪ ለሁሉም ነገር ምህረቱንና ሠላሙን ያውርድልን፤ ይሄን ወረርሽኝም ከሀገራችንና ከዓለምም ያጥፋልንም ነው የምለው”፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this: