Google search engine

“በፊትም ቢሆን ገንዘብን መርጬ እንጂ መጫወት የምፈልገው ለኢትዮጵያ ቡና ነበር” እንዳለ ደባልቄ /ካክሽ/

በመሸሻ ወልዴ /G.BOYS/

የኢትዮጵያ ቡናን በዝውውር መስኮቱ ከባህር ዳር ከተማ ክለብ በመምጣት የተቀላቀለው የአጥቂው ስፍራ ተጨዋች እንዳለ ደባልቄ /ካክሽ/ ከዚህ በፊት ለቡና ለመጫወት ከጫፍ ደርሶ በገንዘብ ክፍያ ባለመስማማት ባይሳካለትም አሁን ላይ ለክለቡ ፊርማውን አኑሮ የቡድኑ ተጨዋች ለመሆን መቻሉ እንዳስደሰተው እየገለፀ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ ቡናው እንዳለ ደባልቄ ወደ ቡና ማምራቱን ተከትሎም ሀሳቡን ሲሰጥ “በፊትም ቢሆን ገንዘብን መርጬ እንጂ መጫወት የምፈልገው ኢትዮጵያ ቡና ነው” በማለትም አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
የኢትዮጵያ ቡናው እንዳለ ደባልቄ በአሁን ሰዓት ከወ/ሮ ቤተልሄም ከተማ ጋር ትዳርን መስርቶ እስጢፋኖስ እንዳለ የተባለ የአራት ዓመትን ልጅ ያፈራ ሲሆን ባለቤቱ አሁን ለኳስ እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረሱ ያበረከተችለትን አስተዋፅኦ ያመሰግናል፤ ይህን ተጨዋች ለቡና በመፈረሙና በሌሎች ጥያቄዎች ዙሪያ አውርተነው የሰጠን ምላሽ በሚከተለው መልኩ ይቀርባል፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡናን በዝውውር መስኮቱ ከባህር ዳር ከተማ ክለብ በመምጣት ልትቀላቀል ችለሃል፤ የእነሱ የቅድሚያ ምርጫህ እንዴት ልትሆን ቻልክ?
እንዳለ፡- ኢትዮጵያ ቡናዎች በቅርብ ጊዜያት ውስጥ የቡድናቸው ተመራጭ ተጨዋች በማድረግ እኔን ወደ ክለባቸው ሊያስመጡኝ የቻሉት አዲሱ አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ሊከተለው ላሰበው የአጨዋወት ፍልስፍናና ወጣ ያለ እንቅስቃሴው አመቺ ትሆናለህ በሚል ነው፤ ለእዚሁ አጨዋወት በማሰብም መጀመሪያ ወደ ቡድኑ እንድመጣ ያደረገኝ አሰልጣኝ ረዳቱ ዘላለም ፀጋዬ /ዞላ/ ነበር፤ እሱን በደንብ ካወራሁት በኋላም ቀጥዬ ከዋናው አሰልጣን ካሳዬ አራጌም ጋር በዋቢ ሸበሌ ሆቴል ተቀጣጥረን ባለኝ የአጨዋወት ዙሪያ ላይ ተነጋግረናል፤ ከእሱ ጋር አውርተን እንደጨረስንም የእኔ ምላሽና ንግግርን አስመልክቶም ወደፊት ሁሉም ነገር በሜዳ ላይ ይታያል ብሎኝ ነው ልንለያይ የቻልነው፤ ከካሳዬ ጋር በነበረን ቆይታ የእኔን ችሎታና ብቃትን በተመለከተ ካሳዬ ወደ ቡድኑ ለመጡት ተጨዋቾች ኃላፊነቱን ከሰጣቸው አሰልጣኖች መካከል አንዱ ረዳቱ ዘላለም ፀጋዬ ነበርና እሱ እኔ ቡናን እንደምጠቅም ስለነገረው ጭምር ነው ለክለቡ ፊርማዬን ለማኖር የቻልኩትና የቡና አመጣጤ ይሄንን ነው የሚመስለው፡፡
ሊግ፡- ለኢትዮጵያ ቡና ልትፈርም በመጣህ ሰአት ከአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ጋር በአንተ የጨዋታ እንቅስቃሴ ዙሪያ በዋቢ ሸበሌ ሆቴል ምን ነበር ለማውራት የቻልከው?
እንዳለ፡- ከኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ጋር ሜዳ ላይ ባለኝ የኳስ ብቃትና እንቅስቃሴ ዙሪያ ያወራሁት እንደ አጥቂ ስፍራ ተጨዋችነቴ ከጓደኞቼ ጋር በአንድ ሁለት ቅብብል ተጫውቼ
ጎል ማስቆጠር የምችል ተጨዋች እንደሆንኩና ከዛ ባሻገርም በጥልቀት ወደኋላ ተመልሼም የአማካይ ስፍራ ተጨዋቾችን እንደማግዝና ከእነሱም ጋር በጋራ የኳስ ቅብብል በመጫወት ወደፊት ለማጥቃት መሄድ የምችል አይነት ተጨዋች እንደሆንኩም ነው የነገርኩት፤ አጨዋወቴን በተመለከተ ከእኔ ውጪም ረዳቱ አሰልጣኝ ዘላለም እኔን ከዚህ በፊት ስጫወት ተመልክቶኝም ነበርና በመጨረሻም በመግባባት ደረጃ ላይ ስለደረስን ነው ለቡና የፈረምኩት፡፡
ሊግ፡- ለኢትዮጵያ ቡና ለመጫወት ከዚህ በፊት ከጫፍ ደርሰህ ሊሳካልህ አልቻለም፤ አሁን ላይ ህልምህ እውን ሊሆን ነው ማለት ነው?
እንዳለ፡- እንደዛ ነው ብዬ አስባለሁ፤ አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ በሜዳ ላይ የሚሰጠውን ልምምድ አሟልቶና በተገቢው መልኩ ለሰራ የቡድኑ ተጨዋች ቅድሚያውን እንደሚሰጥ ስለተናገረና እኔም ደግሞ ያንን የሟሟላት ብቃት አለኝ ብዬ ስለማስብ ነው የመጫወት እድሉን ማግኘቴ አይቀሬ ነው እያልኩ ያለሁት፡፡ የከዚህ በፊቱን የኢትዮጵያ ቡናን የአጭር ጊዜያት የፕረ-ሲዝን ቆይታዬን በተመለከተ በአሰልጣኝ ድራጋን ፖፓዲች ጊዜ ክለቡን ለመቀላቀል ከጫፍ ደርሼና በአሰልጣኙም ተፈልጌ ነበር፤ በጊዜው ግን ከገንዘብ ክፍያ ጋር ባለመስማማት የቡድኑ አባል ሳልሆን ቀርቻለሁ፡፡
ሊግ፡- ወደ ኢትዮጵያ ቡና አሁን ላይ በድጋሚ መጥተሃል፤ ያኔ በገንዘብ ክፍያው ያልተስማማክበት ሂደት ምን ይመስላል?
እንዳለ፡- ያኔ የቡድኑን የፕሪ-ሲዝን ዝግጅት ከተስፋው ቡድን በመምጣት ተቀላቅዬ እየሰራሁ ነበር፤ ሌሎችም ከስር ያደጉ ልጆችም በጋራ አብረውን ይለማመዱ ነበር፤ በጊዜው ዝግጅት ላይ የነበረኝ አቋምና ጥሩ ብቃትም በአሰልጣኙ ፖፓዲች ተወዶልኝ ነበር፤ ከዛ ውጪም በፕሪ ሲዝኑ የተለያዩ የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች ላይም ተጠቅሞብኝ በሀዋሳ ከተማ እና በሲዳማ ቡና ቡድኖች ላይ ጎሎችን እስከማቆጠርለት ደረጃም ላይ ደርሼ ነበር፤ ፖፓዲች በጊዜው ለዋናው ቡድን ሊጠቀምብኝም ከፍተኛ ፍላጎት ነበረው፤ ያም ሆኖ ግን ወደ ዋናው ቡድን በማደጉ ሂደቱ ላይ እኔ የአሰልጣኙ ተመራጭ ተጨዋች ብሆንም ከተስፋ ቡድን ያደግኩና ለክለቡም ሶስት ዓመት ማገልገል ግድ ስላለብኝ በሚከፈለኝ የ800 ብር ደመወዝ ወደ ዋናው ቡድን አድጌ እንድጫወት በወቅቱ በነበረው ስራ አስኪያጁ ገዛኸኝ አማካኝነት ሲነገረኝ በእዚህ መስማማት አልቻልኩም፤ ወዲያውም አሁን ላይ ጥሩ ብቃት ላይ ነው የምገኘው ደመወዜን አስተካክሉልኝና ልደግ የሚል መከራከሪያም ባቀርብ ሊሆንልኝ አልቻለም፤ እነሱም በኋላ ላይ ዝቅተኛ ብር ጨምረውልኝ ለአምስት ዓመት ፈርም ሲሉኝ ልቀበላቸው አልቻልኩምና ከክለቡ መለያየትን መረጥኩ፤ ከዛም ውል ያለብኝ ተጨዋች እንደመሆኔ የውል ማፍረሻ 190 ሺ ብር ከፍዬ ወደ ሀድያ ሆሳህና አመራሁና በእዚህ መልኩ ነበር ከቡና ጋር የተለያየሁት፤ አሁን ላይ ሳስበው ለቡና የመጫወት ፍላጎቴ የነበረው ከበፊት ጀምሮ ነው፤ ያም ሆኖ ግን በጊዜው ገንዘብን ስላስቀደምኩ ነው ከክለቡ ጋር የተለያየሁት፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ቡናን የተስፋ ቡድን በአንድ ወቅት ፎርፌ አስበልተሃል፤ ያኔ ምን ነበር የሆነው?
እንዳለ፡- በጊዜው ኢትዮጵያ ቡናን የተቀላቀልኩት ከደደቢት በመምጣት ነበር፤ ያም ሆኖ ግን በወቅቱ ለቡና ህጋዊ ተጨዋች የሚያደርገኝን ፎርማሊቲ ሙሉ ለሙሉ ባለማወቅ ሳላሟላ ቀርቼ ነበርና ከእነሱ ጋር አካሂደን የነበረውን ጨዋታ ነው የእኔ ተሰልፎ መጫወት ተገቢ ስላልነበር ቡና የፎርፌ ተሸናፊ ሊሆን የቻለው፡፡
ሊግ፡- ወደ ኢትዮጵያ ቡና ከመምጣትህ በፊት ያሳለፍካቸውን የኳስ ጊዜያቶች እንዴት ነው የምትገልፃቸው?
እንዳለ፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ በፕሪምየር ሊግ ደረጃ ለዋናው ቡድን ተሰልፌ የተጫወትኩባቸው ክለቦች ሀድያ ሆሳዕና፣ ጀማ አባጅፋርና የባህር ዳር ከተማ ክለቦች ቢሆኑም ለእኔ ጥሩ ጊዜን ተሰልፌ እስከመጫወት ድረስ ያሳለፍኩበት ቡድን ቢኖር ሀድያ ሆሳዕና ነው፤ እዚያ ለሁለት አመት ያህል በቋሚ ተሰላፊነት ጭምር ነው የተጫወትኩትና ይሄ የማይረሳኝ ነው፡
ሊግ፡- የጅማ አባጅፋርና የባህር ዳር ከተማ ክለቦች ቆይታህስ?
እንዳለ፡- ብዙም የመጫወት ዕድሎችን ያገኘሁባቸው ክለቦች ስላልሆኑ በመልካምነት የምጠቅሳቸው አይደሉም፤ ወደ ጅማ አባጅፋር ስመጣ በአሰልጣኝ ገ/መድህን ሃይሌ ተፈላጊነት ነበር፤ የዛ ቡድን ቆይታዬና አጀማመሬ ጥሩ የነበረ ቢሆንም በኋላ ላይ በእግሬ ላይ የደረሰብኝ ጉዳት ለ8 ያህል ጨዋታዎች ብቻ ክለቤን እንዳገለግል ስላደረገኝ ያ ብዙም ምቾት እንዲሰማኝ አላስቻለኝም፤ የጅማ ቆይታዬ ላይ ለእኔ ጥሩ ነበር ብዬ የምጠቅሰው ከቡድኑ ጋር የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት የቻልኩበትን ወቅት ብቻ ነው፤ የባህር ዳር ከተማ ቆይታዬ ደግሞ በአሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ማንጎ ላይ ይደርሱበት በነበሩት ተፅህኖዎች ምክንያት የመጫወት እድልን ካለማግኘት ጋር ሌላው መልካም ጊዜን ያላሳለፍኩበት ቡድን ነውና ይሄን ነው ማለት የምፈልገው፡፡
ሊግ፡- በኢትዮጵያ ቡና የዘንድሮ ቆይታ የተሳካና ጥሩ ጊዜን የምታሳልፍ ይመስልሃል?
እንዳለ፡- አዎን፤ በቅድሚያ ለቡና የምጫወትበትን እድል ያገኘሁበት አጋጣሚ ስለተፈጠረልኝ በጣም ደስ ብሎኛል፤ ያኔም ቢሆን ገንዘብን ስላስቀደምኩ እንጂ ለቡና መጫወት ነበር የምፈልገውና በቡና ቆይታዬ ዘንድሮ የተሳካና ጥሩ ጊዜን የማሳለፍ ይመስለኛል፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ቡና የፕሪ ሲዝን ዝግጅት ምን ይመስላል?
እንዳለ፡- ኢትዮጵያ ቡና በአዲሱ አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ የጀመረው የፕሪ ሲዝን ዝግጅትና ስልጠና በጣም ጥሩና የወደድነው ነው፤ የ3 ቀን ያህል ልምምድንም እስካሁን ሰርተናል፤ በአሰልጣኙ እየተሰጠን ያለው የዝግጅት ጊዜ ልምምድም ከዚህ በፊት ብዙ አሰልጣኞች እንደሚያሰሩት መውደቅና መነሳትን ሳይሆን ከኳስ ጋር የተያያዘ ነው፤ በሚያምርና ደስ በሚል መልኩም ነው ስራችንን እየሰራን የምንገኘው፤ የአሰልጣኙን ልምምድ ሳየው እስከዛሬ ድረስ ኳሱን በደንብ እንዳልቻልንና ከዜሮ በመነሳትም መለማመድ እንዳለብንም ነው የተረዳሁትና ልምምዱ አስደስቶኛል፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ቡና ስብስብን እንዴት አገኘኸው?
እንዳለ፡- ኢትዮጵያ ቡና አሁን የያዘው የተጨዋቾች ስብስብ ጥሩ ነው በአብዛኛውም በመካከለኛው እድሜ ላይ የሚገኙ ጥሩ ችሎታ ያላቸውን ልጆችም ይዟል፤ እነዚህ ተጨዋቾችም በተለይ ደግሞ የአዲሱን አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌን የጨዋታ ፍልስፍና በደንብ እና በአግባቡ መከታተል ከቻሉ ለክለቡ ብቻ ሳይሆን ለሃገርም ብዙ ነገሮችን መስራት እንደሚችሉ ተመልቻለሁና በስብስቡ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና ዘንድሮ ምን ውጤትን ያመጣል?
እንዳለ፡- ኢትዮጵያ ቡና 2003 ላይ ዋንጫ ሲያነሳ የክለቡ ደጋፊ ነበርኩ፤ ያንን ድል አሁን ላይ በተጨዋችነቴ ማሳካት እፈልጋለሁና ዘንድሮ ቡና ስኬታማ ውጤት ያመጣል፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this: