Free Porn
xbporn

buy twitter followers
uk escorts escort
liverpool escort
buy instagram followers
6x games unblocked fnaf unblocked games 76 unblocked games krunker.io slither unblocked io premium unblocked github.io unblocked games
Google search engine

“ኢትዮጵያ ቡናን ያለ ደጋፊው ሲጫወት ማየት ኳስ ውበቷን አጣች እንደ ማለት ነው” አማኑኤል ዮሃንስ /ኢትዮጵያ ቡና/

“ለኢትዮጵያ ቡና እንደተጫወትኩ ጫማዬን ብሰቅል በጣም ደስ ይለኛል”
“ኢትዮጵያ ቡናን ያለ ደጋፊው ሲጫወት ማየት ኳስ ውበቷን አጣች እንደ ማለት ነው”
አማኑኤል ዮሃንስ /ኢትዮጵያ ቡና/


የኢትዮጵያ ቡና ስኬታማ የአማካይ ስፍራ ተጨዋች ነው፤ ቡድኑንም በካፒቴንነት በመምራት ይታወቃል፤ ይሄ ተጨዋች አማኑኤል ዮሃንስ ሲባል ከኮቪድ 19 በኋላ ጊዜውን በምን መልኩ እያሳለፈ እንደሆነ፣ የውል ዘመኑን በቅርቡ የሚጨርስ ስለመሆኑ፣ ስላሳለፈው አንድ አንድ የእግር ኳስ ጊዜያቶቹና ሌሎች ከእሱ ጋር የሚያያዙ ተጨማሪ ጥያቄዎችን የሊግ ስፖርት ጋዜጣ አዘጋጅ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ አቅርቦለት ምላሹን እንደሚከተለው ሰጥቷል፤ ተከታተሉት፡፡


በኮቪድ 19 ለወራቶች ከእግር ኳስ ስለመራቁ እና በውስጡ ስለተፈጠረበት ስሜት


“የእግር ኳስ ጨዋታ መዝናኛዬ፣ ስራዬ እና ዘወትርም የምንቀሳቀስበት የስፖርት አይነት በመሆኑ ከእዚህ ከምወደው እና በጣምም ከማፈቅረው ሙያዬ ለወራቶች ያህል ለመራቅ በመቻሌ የተፈጠረብኝን ስሜት ከባድ ሆኖ ነው ያገኘሁት፤ ኮቪድ 19 ዓለምን ያስጨነቀ ወረርሽኝ ነው፤ በእዚሁም ምክንያት ከእግር ኳሱ የራቅነው እኛ ብቻ አይደለንም፤ መላው ዓለምም ነበር ከኳሱ የራቀው፤ ይሄ ደግሞ ለሁላችንም ግዴታም ነበር፤ ያለ ኳስ ለረጅም ጊዜ የማሳለፍ ስሜቱን ደግሞ ሁሉም ሰውም በሚገባ ቀምሶታል፤ ስለዚህም የእግር ኳስ ጨዋታ ምን ያህል ተወዳጅና ደስታንም ይሰጥ እንደነበርም ስለተረዳንና አሁን ላይም ምንም ነገርን ለማድረግም ስለማንችል ለወደፊቱ የሀገራችን የሊግ ውድድር በመጪው ዓመት ስለሚጀመርበት ሁኔታ ነው ነገሮችን በትዕግስት ልንጠብቅ የሚገባን፤ ፈጣሪም ወደምንወደው ሙያችን እንዲመልሰን ልንፀልይም ይገባል”፡፡


ከዚህ ቀደም ከእግር ኳስ ለእዚህን ያህል ጊዜ ርቆ እንደሆነ


“በፍፁም፤ በእዚህ መልኩ ከኳስ ስርቅ የአሁኑ የመጀመሪያዬ ነው፤ ያውም በውድድር ላይ ብቻ ሳይሆን በሰፈር ደረጃም በማትጫወትበት ሁኔታም ላይ በምትገኝበት የአሁን ሰዓት፤ ይህ ደግሞ ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ተጨዋቾችም የመጀመሪያቸው ስለሚሆንም ያ ሁላችንን ተመሳሳይም ያደርገናል”፡፡


ከኮቪድ 19 በኋላ እንደ አንድ እግር ኳስ ተጨዋች ወቅቱን በምን መልኩ እያሳለፈ እንደሆነ


“በጣም አስገዳጅ ሁኔታዎች ካልተፈጠሩ በስተቀር ከቤት ውስጥ ባለመውጣት ነው የተለያዩ የስፖርት እንቅስቃሴዎችን በመስራት ጊዜዬን የማሳልፈው፤ እነዚህም እንቅስቃሴዎቼ አንድአንዶቹ በፊልም ደረጃ ካገኘዋቸው የምሰራቸው ሲሆኑ አንድአንዶቹ ደግሞ በአሰልጣኛችን አማካኝነት በሜዳ ላይ የሚሰጠንን ልምምዶችን ነው የምሰራው፤ ከዛ ውጪ ደግሞ በቤት በምቀመጥበት ሰዓት ደግሞ የተለያዩ የአማርኛ ፊልሞችን እመለከታለው፤ ፕሌይስቴሽንም እጫወታለው”፡፡


ቤተሰቦችህን ለእንደዚህን ያህል ጊዜ በተደጋጋሚ ለማግኘት በመቻልህ ስለፈጠረብህ ስሜት


“በእርግጥ ቤተሰቦቼን ከዚህ ቀደምም ቢሆን እዚሁ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እንደመኖሬ እና ከእነሱም ብዙ ያራቅኩበት ሁኔታ በመኖሩ በቅርብ የማገኛቸው ቢሆንም የአሁኑን ግን ለየት የሚያደርገው ነገር ቢኖር ዕለት ከዕለት ስለማገኛቸው እና ስለ ወደፊቱ አኗኗራችንም ብዙ ነገሮችን ተገናኝተን ስለምንነጋገር እነሱን በዚህ መልኩ ሳገኛቸው በጣም ነው ደስ የሚለኝ”፡፡


ቤተሰቦችህ የአሁን ሰዓት ላይ ለአንተ ያላቸው አጋርነት


“ባይገርምህ ወላጅ እናቴ የእግር ኳሱ ስራዬና እንጀራዬ ስለሆነ እንጂ ከእዚህም በኋላ ሁሌም ቢሆን ከአጠገቤ ባትለየኝ በጣም ደስ ይለኝም ነበር ያለችኝ፤ ይህ ማለት እሷ ለእኔ ያላትን ከፍተኛ ፍቅርና ሀሳቢነቷንም ጭምር ነው ያሳየኝ፤ ከዛ ውጪም እናቴን ጨምሮ ሌሎቹም ቤተሰቦቼም በእዚህ ሰዓት ለእኔ የሚያደርጉልኝ እገዛ ከፍተኛ ነው፤ ስለዚህም አሁን ብቻ ሳይሆን ከዛ በፊትም በኳሱ ዛሬ ላይ ለደረስኩበት ደረጃ የእነሱ አጋርነት ከፍ ያለም ስለሆነም በጣሙን ላመሰግናቸው እፈልጋለው”፡፡


በቤተሰባችሁ ውስጥ ወሳኝ እና መሪው ሰው ማን እንደሆነ


“የመጀመሪያዎቹ ወላጆቼ ናቸው፤ ከዛ በኋላ ደግሞ አንድ ወንድም እና ሁለት እህቶች ያሉኝ ቢሆንም እንደታላቅነቴ ቀጥዬ ቤቱን የምመራው እኔው ነኝ””፡፡


ቤተሰቦችህ የእግር ኳስ መጫወትህን ለኢትዮጵያ ቡና የዋናው ቡድን እስክትገባ ድረስ አያውቁም ስለመባሉ


“የእውነት ነው፤ ያኔ እነሱ ትምህርቴን ብቻ እንደምማር ነው የሚያውቁት፤ ኳስ ተጨዋች ሳይሆን ጥሩ ተማሪ እንድሆንም ነበር የሚፈልጉት፤ በጊዜው ግን እኔ ለቡና የተስፋ ቡድን ኳስን እጫወት ነበር፤ ከቤት ስወጣም ትጥቄን በቦርሳዬ ይዤም ነበር ወደ ትምህርት ቤት የምሄደው፤ በእንዲህ መልኩም ነው ኳሱን ከተጫወትኩ በኋላ ወደዋናው ቡድንም ያደግኩት፤ ያኔም ነው ኳስ ስለመጫወቴ ሲረዱ ከእኔ ጎን በመሆን በብዙ ነገሮች ቤተሰቦቼ ያግዙኝ የነበሩት”፡፡


ወደ እግር ኳስ ተጨዋችነቱ ዓለም ባትመጣ ኖሮ ምን ሆነህ እናገኝህ ነበር?


“ምንአልባት በትምህርቴ ገፍቼ እና ጥሩ ተማሪም ሆኜ በመመረቅ በአንድ ድርጅት ውስጥ ተቀጥሬ ሰራተኛ እሆን ነበር”፡፡
ሽሮ ሜዳ አንተን ያፈራች ሰፈር ናት፤ ስለ አካባቢዋ ምን ትላለህ?
“ሽሮ ሜዳን ምን ብዬ እንደምገልፅልህ አላውቅም፤ ከእኔ ውጪ ብዙ የሀገሪቱን ታዋቂ የእግር ኳስ ተጨዋቾች ያፈራች ሰፈር ናት፤ ከእነዛ ውስጥም እንደ እነ ታፈሰ ተስፋዬን፣ ተክሉ ተስፋዬን ተሾመ ሆሼንና ሌሎችንም ተጨዋቾች መጥቀስ ይቻላል፤ ከእዛ ውጪ ጥሩ ማህበረሰብ የወጡባት፣ ልዩ እና ደስም የምትል ሰፈር ናትና ሁሌም ቢሆን ትናፍቀኛለች”፡፡


ሽሮ ሜዳ በዋናነት ስለምትታወቅበት ሁኔታ እና ሰፈሯን በአጭር ቃላት ግለፃት ብትባል


“ሽሮ ሜዳ ለየት ባለ መልኩ የምትታወቀው በሀገር ባህል ልብሶችና ምርቷ ነው፤ ብዙዎች እንደውም የሀገር ባህል ልብሶች ምስረታውም እስከፍፃሜውም እዚህም ነው በሚል ሰፈሯን በልዩ መልኩም ይገልጿታል፤ እሷ በአጭሩ ስትገለፅም በቃ ልዩ ሰፈርና በጣምም የምትወደድ ናት”፡፡


በአሁን ሰዓት በዋናነት የናፈቀህ ነገር ቢኖር


“ምንም ጥያቄ የለውም የእግር ኳስ ጨዋታ በጣም ናፍቆኛል”


ለኢትዮጵያ ቡና ከተስፋ ቡድን አንስቶ እየተጫወተ ስለሚገኝበት ሁኔታ


“ኢትዮጵያ ቡና ማለት ለእኔ በጣም የምወደው ክለቤ ነው፤ ለቡድኑ ጥልቅ የሆነ ፍቅርና ትልቅም የሆነ ክብርና ቦታ አለኝና ለእዚህ ቡድን እስካሁን ድረስ እየተጫወትኩ ባለሁበት ሁኔታ በጣሙን ደስተኛ ነኝ”፡፡


አንድ አንድ የእግር ኳስ ተጨዋቾች የእግር ኳስን በጀመሩበት ክለብ ተጫውተው በእዛው ቡድን ያቆማሉ፤ አንድ አንዶቹ ደግሞ ክለብ ይቀያይራሉ፤ አማኑኤልንስ ከእዚህ አንፃር በምን ደረጃ እንጠብቀው?


“የእግር ኳስን በቡና ማልያ እንደጀመርኩ በቡና ማልያ ባቆም በጣም ነው ደስ የሚለኝ፤ ይሄ ቢሆንና ቢሳካልኝም ከፍተኛ ምኞቴ ነው፤ ያም ሆኖ ግን የእዚህን መልስ በሂደት የምናየው ነገር ነው”፡፡


ለኢትዮጵያ ቡና መጫወት የልጅነት እልምህ ነበር?


“በጣም፤ ይህን ያልኩት ያለ ምክንያትም አልነበረም፤ ለቡድኑ መጫወት የሁልጊዜም እልሜም ነበር፤ ይሄ ሊሆን የቻለውም ክለቡ ትልቅ ስለሆነና በብዙዎች ዘንድ የሚወደድም ስለሆነ ነው፤ ከዛ ውጪም በዛ አስገራሚ እና ምርጥ ደጋፊ ፊት ኳስን እየተጨፈረልህ መጫወትም የተለየ አይነት የደስታ ስሜትን ስለሚሰጥ ከልጅነቴ ዕድሜ አንስቶ ነው ለክለቡ መጫወትን ያለምኩትና በመጫወቱም በጣም ደስተኛ የሆንኩትና ሊሳካልኝም የቻለው”፡፡


የእግር ኳስን ልጅ ሆኖ ሲጫወት ለእሱ ተምሳሌት ስለነበረው ተጨዋች


“የእግር ኳስን መጫወት ስጀምር ለእኔ ተምሳሌቴ እና ሮል ሞዴሌ የነበረው ተጨዋች የሰፈራችን ልጅ የሆነው ውጤታማው አጥቂ ታፈሰ ተስፋዬ ነበር፤ ታፌን በጊዜው ሲጫወት ላደንቀው የቻልኩትም ከሰፈር አንስቶ እስከ አዲስ አበባ ስታድየም ድረስ እመለከተው ስለነበር እና አጨዋወቱም የሚስበኝ ስለነበር ነው፤ እሱን እንዳደነቅኩት ሁሉ ከባህር ማዶ ተጨዋቾች ደግሞ በጣም የማደንቃቸው ተጨዋቾች የአርሰናል ደጋፊ እንደመሆኔ ፋብሪጋስን እና ሜሱት ኦዚልን አደንቃቸዋለው፤ የሁለቱ አጨዋወትም በጣም ይስበኝም ነበር”፡፡


የታፈሰ ተስፋዬ አድናቂ ሆነህ አድግሃል፤ አሁን ላይ አንተ ለደረስክበት ደረጃ እሱስ ከልምዱ አንፃር የነገረ የተለየ ነገር ይኖራል?


“አዎ፤ አልፎ አልፎ ከእሱ ጋር እናወራለን፤ በኳሱ ጥሩ ደረጃ ላይ መድረስን ካለምክ ይሄን አድርግ፤ የምትጫወተው በትልቅ ክለብ ውስጥ ነው በሚል እና ሌሎችንም ነገሮች በመጥቀስ ካለው ልምድ አንፃርና እንደ ታላቅነቱም የሚነግረኝ በጣም ጠቃሚ እና ጥሩ ጥሩ ነገሮችም ስላሉ እገዛው ጠቅሞኛል፤ ታፌን በእዚሁ አጋጣሚ ላመሰግነውም እፈልጋለው”፡፡


ለኢትዮጵያ ቡና ካደረግካቸው ግጥሚያዎች ለአንተ የምንግዜም ምርጡ


“በቀዳሚነት ደረጃ የማስቀምጠው ምርጡ ጨዋታዬ ከዓመታት በፊት ከደደቢት ክለብ ጋር ያደረግነውን ነው፤ ያ ጨዋታም በሳዲቅ ሴቾ ሶስት ግቦች አሸንፈን የወጣንበትም ነበር፤ እኔም በጨዋታው በጣም ጥሩ ተንቀሳቅሼበት ስለነበር ይሄን ግጥሚያ መቼም ቢሆን አልረሳውም”፡፡


በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመንህ ምርጧ ግብህስ


“ምርጧ ግቤ ኢትዮጵያ ቡና በአበበ ቢቂላ ስታድየም ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ሲጫወት ያስቆጠርኳት ናት፤ ያኔ በእኔ ብቸኛ ግብ ጨዋታውንም 1-0 ለማሸነፍ ችለንም ነበር”፡፡


ኮቪድ 19 ከገባ በኋላ ለመጨረሻ ጊዜ ተመልክተከው የናፈቀህ ሰው አለ?


“አዎን፤ የናፈቁኝ ሁሉም የቡድኔ ተጨዋቾች እና አባላቶች ናቸው፤ ምክንያቱም ሁሌም ከእነሱ ጋርም ነበር የምውለውና”፡፡


በባህር ማዶ የእግር ኳስ ውድድሮች ስለመጀመራቸው እና ስለ እኛም ሀገር ኳሱ ስለሚጀመርበት ሁኔታ


“በአሁን ሰዓት የዓለም እግር ኳስ ወደነበረበት ውድድር በመመለሱ ለእኛም ሀገር ቢሆን ትንሽ ተስፋን ሰጥቶናል፤ ይሄ መሆን መቻሉም የሚያስደስት ነገር ነው፤ እነሱ የእግር ኳስ ውድድራቸውን ሊመልሱት የቻሉት ከመንግስት እና ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በሚተላለፍላቸው መመሪያ መሰረት አስፈላጊውን ጥንቃቄም ስለሚያደርጉ ነው፤ ስለዚህ እኛም ከእነሱ በመማር እና ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግ ይሄንን ከባድ ጊዜም በማለፍ ወደ እግር ኳሱ ዳግም እንድንመለስ ፈጣሪ ይርዳን ነው የምለው”፡፡


በኮቪድ 19 ምክንያት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ያለ ደጋፊዎች ቢጀመርና ቡናም በእዛ መልኩ ቢጫወት የሚኖሩት ሁኔታዎች ምን የሚሆን ይመስልሃል?


“ኢትዮጵያ ቡናን ያለ ደጋፊው ሲጫወት ማየት ኳስ ውበቷን አጣች እንደ ማለት ነው፤ ስለዚህም ቡናን ያለ ደጋፊው ማየት በጣም ከባድም ነገር ስለሆነ ይሄ ወረርሽኝ ጠፍቶ የእኛም ክለብ ሆነ ሌሎቹ ቡድኖች በደጋፊዎቻቸው ፊት የሚጫወቱበት ሁኔታ እንዲፈጠር ከፍተኛ ምኞት ነው ያለኝ”፡፡


በእግር ኳስ ተጨዋችነት ህይወትህ ደስተኛ ነህ?
“በጣም፤ ሁሌም ደስተኛም ነኝ”፡፡


በኳስ ህይወትህ ተከፍተህስ ታውቃለህ?


“አዎን፤ እነዛ የተከፋሁባቸው አጋጣሚዎችም አንዱ ከዓመታት በፊት ማለትም 2010 ላይ ወደ ዋንጫው ፉክክር እያመራን በነበርንበት ሰዓት ላይ በዝናባማው እና ጨቅይቶ በነበረው የአዲስ አበባ ስታድየም ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ስንጫወት ነጥብ ጥለን ከዋንጫው ፉክክር የወጣንበት ሁኔታ እና ሌላው ደግሞ ከሐዋሳ ከተማ ጋር ስንጫወት መስዑድ ባስቆጠረው ግብ አሸነፍን ብለን ስንጨፍር ወዲያው ግብ ገብቶብን አቻ የወጣንበት ጨዋታ በጣም ያስከፋኝ ነው፤ ሌላው ደግሞ ከቡና ጋር በተለይ ደግሞ ከእዚህ ምርጥ እና በጣምም ከምወዳቸው የክለቡ ደጋፊዎች ጋር በጋራ ሆኜ የሊግ ዋንጫውን አለማንሳት መቻሌም ያስቆጨኛል”፡፡


በኢትዮጵያ ቡና ውልህን ልትጨርስ ተቃርበሃል፤ ከክለቡ ጋር ትቀጥላለህ?


“ከክለቡ ጋር ብቀጥል ደስ ይለኛል፤ ያም ሆኖ ግን ውሌን ሰኔ 30 ስለምጨርስ መቀጠሌ እና አለመቀጠሌ በጊዜ የሚታይ ይሆናል”፡፡


በእግር ኳስ ተጨዋችነትህ የምትፈልግበት ደረጃ ላይ ደርሰሃል?


“አልደረስኩም፤ እነዛን ለማሳካትም ብዙ የማስባቸው ነገሮች አሉ፤ ቢሳካልኝ እና ቢሆንልኝ ከሀገር ውጪ የመጫወት ከፍተኛ ፍላጎቱ አለኝ፤ ያን ለማሳካትም እየጣርኩ ነው ያለሁት”፡፡


ስለ ብሔራዊ ቡድን የቀጣይ ጊዜ ተሳትፎን በተመለከተ


“ለረጅም ዓመታት በተደጋጋሚ ጊዜ ተመርጦ ስለመጫወትን አስባለው፤ ለእዛም ሁሌም ጠንክሬ እሰራለው”፡፡


በሀገር ውስጥ እና በውጪ ሀገር አሰልጣኞች መካከል በመሰልጠን ስላለው ልዩነት በተለይ በካሳዬ ሰልጥንሃልና ከእሱ ጋር ስታነፃፅራቸው


“በብዙ ማለትም ሶስት በሚደርሱ የውጪ ሀገር አሰልጣኞች ሰልጥኛለው፤ እነሱን ስመለከት በሚያሰሩት ስራ ከእኛ አሰልጣኞች ጋር ሳስተያያቸው በጣም ነው ልዩነት ያላቸው፤ በተለይ ደግሞ ከካሳዬ ጋር ያለውን ሁኔታ ሳይ ካሳዬ ኳስን እንዴት አድርገህ መጫወት እንዳለብህ ያሳይሃል፤ የራሱም የስልጠና መንገድ አለው፤ በስራው አንዴት ለሚለው ጥያቄ መልስም ይመልስልሃል፤ መልሶቹም አሪፍ ናቸው፤ የትም ብትሄድ የራሱ ፍልስፍናና ወጥ የሆነ አቋምም አለው፤ ሁሌም አህምሮህን ነው የሚያሰራህ፤ የውጪዎቹ ደግሞ ፊዘካል ላይ ነው የሚያሰሩህና የእሱን ስልጠናና በኳሱ ሳይ ያለውን አመለካከት ሳይ ለየት እንዲልብኝም አድርጎብኛል፤ የሚያሰራውም ስራ አዲስ ፍልስፍናም ስለሆነ ደስ በሚል ሁኔታ እየሰራንም ብዙ ለውጦችንም በችሎታችን ላይ ልናመጣም ችለናል”፡፡

እንደ ቡና ካፒቴንነትህ ከካሳዬ አራጌ ጋር የምትገናኝበት አጋጣሚዎች አሉ?


“አዎን፤ እሱ በአሁን ሰዓት በአሜሪካ ሀገር ነው የሚገኘው፤ ስለ ቡድኑ ተጨዋቾችም ሁኔታ ይጠይቀኛል፤ የሰላምታ መልህክቱንም እንዳደርስለትም ያናግረኛል፤ እንዴት ናቸው? ከክለቡ ጋር በተያያዘም አስፈላጊ የሚባሉ ጥያቄዎችንም የሚያቀርቡም ካሉ አውራቸው ብሎም ደስ በሚል ወንድማዊ በሆነ ሁኔታም እያናገረኝ ይገኛልና እስከዚህ ድረስ ነው ጥሩ ግንኙነት ያለን”፡፡


የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ከተጨዋቾች የደመወዝ ክፍያ ጋር በተያያዘ የምትለው ነገር ካለ


“ከአንድ አንድ ክለቦች ጋር በተያያዘ የአሁን ሰዓት ላይ ቡድኖቹ ለተጨዋቾች ደመወዝ አለመክፈል መቻላቸው ትክክል ያልሆነ እና በጣምም የሚከብድ ነገር ነው፤ ምክንያቱም አብዛኛው ተጨዋች ትዳር ይዞ የሚኖርና ቤተሰቡንም ጭምር የሚረዳም ስለሆነ ነው፤ በዛ ላይ ልጅ ያላቸው ተጨዋቾችም አሉና ያን እያዩ ዝም ማለት ተገቢ አይደለም ስለዚህም በፍጥነት ክፍያውን ሊፈፅሙላቸው ይገባል፤ የእኛን ክለብ ጨምሮ ደግሞ ሌሎች ደመወዝ ለሚከፍሉ ክለቦች ደግሞ ምስጋናዬን ማቅረብ እፈልጋለው”፡፡


በመጨረሻ
“የእግር ኳስ ውድድራችን ዳግም እንዲጀመር ሁላችንም አሁን ላይ ከባድ ከሆነው ወረርሽኝ ለመላቀቅ ከእኛ የሚጠበቀውን አስፈላጊ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባናል፤ ከዛ ውጪም ሌላ ለመናገር የምፈልገው ነገር ቢኖር የፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ማህበርም ለተጨዋቾች ለመቆም የመጡበት ሁኔታ የሚያስደስትም ነገር ነውና በዚሁ ሊቀጥሉ ይገባል፤ እኛ ተጨዋቾችም እነሱን ልናግዛቸው ይገባል”፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

P