የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ለሚመራው ኢትዮጵያ መድን በወጣትነቱ ዕድሜ በመጫወት ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴን በማሳየት ላይ ይገኛል።
ይህ የግራ መስመር የኮሪደር ስፍራ ተጨዋች ያሬድ ካሳዬ ሲባል ስለ ኢትዮጵያ መድንና ስለራሱ እንደዚሁም ደግሞ በሌሎች ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ከሊግ ስፖርት ጋዜጣ አዘጋጅ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ ጋር ቆይታን አድርጎ ተከታዩን ምላሽ ሊሰጠን ችሏል፤ ቃለ-ምልልሱን ተከታተሉት።
ሊግ፦ በቅድሚያ ለቃለ ምልልሱ ፍቃደኛ ስለሆንክ ከልብ እናመሰግንሃለን?
ያሬድ፦ እኔም የጋዜጣችሁ እንግዳ ስላደረጋችሁኝ አመሰግናችኋለሁ።
ሊግ፦ ውልደትህና እድገትህ የት ነው?
ያሬድ፦ የተወለድኩት በአርባምንጭ ከተማ ምዕራብ አባይ አካባቢ ነው፤ በሶስት ዓመቴም ወደ አዲስ አበባ ከተማ በመምጣት በኮልፌ አካባቢ ላድግም ችያለሁ።
ሊግ፦ ወደ እግር ኳስ ተጨዋችነቱ ዘልቀህ ስትገባ ማንን ተምሳሌት /ሮል ሞዴል/ ለማድረግ ቻልክ?
ያሬድ፦ ምንም እንኳን የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊ የነበርኩ ቢሆንም የእኔ ተምሳሌት ተጨዋች የነበረው አሽሊ ኮል ነው፤ ከሀገር ውስጥ ተጨዋቾች ደግሞ በአሁን ሰዓት በግብፅ ሊግ በመጫወት ላይ የሚገኘው የሽመልስ በቀለ እና በቦታዬ ከሚጫወቱት ተጨዋቾች መካከል ደግሞ የብርሃኑ ቦጋለ /ፋዲጋ/ አድናቂ ስለሆንኩኝ እነሱ ተምሳሌቶቼ ናቸው።
ሊግ፦ በልጅነትህ ዕድሜ ወደ አዲስ አበባ መምጣትህን ተናግርሃል፤ ምክንያትህ ምን ነበር?
ያሬድ፦ የመጣሁበት ዋናው ምክንያት የአያቴ እህት አዲስ አበባ ነበረች፤ እኔ ባለሁበት አርባምንጭ ከተማ ደግሞ በጊዜው የኑሮ አለመመቸት ነበረና እናቴ ወደ አያቴ እህት ጋር በመሄዷ በእዚህ መልኩ አብረን ለመኖር ቻልን።
ሊግ፦ በቤተሰባችሁ ውስጥ ስንት ወንድምና እህት አለ? ስፖርተኛውስ አንተ ብቻ ነህ?
ያሬድ፦ በቤት ውስጥ ካለነው ከሆነ ስፖርተኛው እኔ ብቻ ነኝ፤ ከእዛ ውጪ ከሆነ ደግሞ አያቴ ተፈራ ቡልቲ ኳስ ተጨዋች ነበር። ሌላው ደግሞ ስለ ቤተሰቤ ለጠየቅከኝ ሶስት ታናናሽ እና በጣም ህፃናት የሆኑ ወንድሞችም ነው ያሉኝ።
ሊግ፦ በልጅነትህ የእግር ኳስ ተጨዋች ሆነህ አደግክ፤ ኳስ ተጨዋች ባትሆን ኖሮስ?
ያሬድ፦ ወላጅ አባቴ በጋራዥ ሰራተኝነት ስላሳለፈና እኔም ወደ መኪናው ዘርፍ አደላ ስለነበር ያኔ ኳስ ተጨዋች ባልሆን ኖሮ መካኒክ እሆን ነበር።
ሊግ፦ የፕሪምየር ሊጉን ዘንድሮ ለተቀላቀለው ለኢትዮጵያ መድን በመጫወት ላይ ትገኛለህ፤ አሁን ያለህበትን የብቃት ደረጃ በምን መልኩ ትገልፀዋለህ?
ያሬድ፦ በእግር ኳሱ አሁን የምገኝበትን ደረጃ ገና ነኝ ብዬ ነው የማስበው፤ ኳሱንም አልጀመርኩትም፤ በቀጣይነት ግን አሰልጣኝ ገብረመድህን ሀይሌ የመሰለፍ ዕድሉን እየሰጠኝ በመሆኑ ቡድኑን ከመጥቀም ባሻገር ራሴንም ከፍ ባለ ደረጃ የማገኘው ያህል ነው የሚሰማኝ።
ሊግ፦ ኮልፌን በልጅነትህ ዕድሜህ አደግክባት፤ መኖሪያ ሰፈርህን በአጭሩ ስትገልፃት?
ያሬድ፦ ሰፈሩ ለስፖርተኛውም ሆነ ለነዋሪው ምርጥ አካባቢ ነው፤ እንደ መላጣና አስፋውን የመሳሰሉ ምርጥ ሜዳዎችም አሏትና የእዚህ አካባቢ ልጅ መሆኔ ዔድለኛ ያደርገኛል።
ሊግ፦ የእግር ኳስን መጫወት የጀመርከው በፕሮጀክት ደረጃ ወይንስ በክለብ?
ያሬድ፦ ይገዙ ሻንቆ የሚባል የፕሮጀክት ቡድን ነበር። እሱም ጋር ነው ኳስን መጫወት የጀመርኩት፤ በኋላ ላይ ወደ ክለብ ተተኪ ቡድን ተጨዋችነት ያን ጊዜ በካሊድ መሀመድ ይሰለጥን ወደ ነበረው ወደ መድን በማምራት እዛ መጫወትን ጀመርኩኝ።
ሊግ፦ ግራኝ ተጨዋች ነህ፤ ቀኝህስ?
ያሬድ፦ እሱን ብዙም አልጠቀምበትም። በግራ እግሬም ነው የምጫወተው።
ሊግ፦ የኢትዮጵያ መድን ቆይታህ በምን መልኩ ይገለፃል?
ያሬድ፦ ከስር በእያንዳንዱ ዓመት ላይ ነው ወደ ላይ ያደግኩት። ካደግኩ በኋላም የመጫወት ዕድሉን አሁን ላይ አሰልጣኜ እየሰጠኝ በመሆኑ ቆይታዬ ጥሩ የሚባል ነው።
ሊግ፦ የኢትዮጵያ መድንን ዋና ቡድን መች ተቀላቀልክ?
ያሬድ፦ በ2012 ነው። በከፍተኛው ሊግ ላይ ስጫወት ከቆየው በኋላም ዘንድሮ ወደ ፕሪምየር ሊግ በማደግ እየተጫወትኩ እገኛለሁ።
ሊግ፦ ኢትዮጵያ መድን በእግር ኳሱ ስላለው ስምና ዝና የቱን ያህል ታውቃለህ?
ያሬድ፦ ስለዚህ ቡድን ብዙ ያወቅኳቸው ነገሮች አሉ። ከእነዛም መካከል ብዙ ወጣት ተጨዋቾችን ለሀገር እግር ኳስ ጭምር ያፈራና በወጣቶችም ላይ የሚያምኑ ስለመሆኑ አሁን በቡድኑ ውስጥ በአሰልጣኝነት ካሉት መካከል እነ ሀሰን በሽርና መስፍን አህመድ /ጢቃሶ/ የእዚህ ቡድን የቀድሞ ተጨዋቾች ስለመሆናቸው ሌላው ደግሞ በአፍሪካ ክለቦች የካፍ ካፕ ውድድርም በጥሩ ጉዞ ለፍፃሜ ጨዋታ ለመቅረብ ከጫፍ ደርሶ የነበረ ስለመሆኑ እና ታላቅ ክለብም እንደነበር ይህንን በመጠኑ አውቃለሁ።
ሊግ፦ ለኢትዮጵያ መድን መጫወት ምን ስሜት ይሰጣል?
ያሬድ፦ በቅድሚያ ይህ ክለብ የሀገሪቱ ምርጥ በመሆኑ ማሊያውን ለብሼ በመጫወቴ ኩራት ይሰማኛል። ለቡድኑ ተጫውቼለትም ምርጥ የሆነ ግልጋሎትን ልሰጥለትም ዝግጁ ነኝ።
ሊግ፦ የኢትዮጵያ መድንን ከስምንት ዓመታት በኋላ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለማስገባት ያደረጋችሁት ጥረት ምን ይመስላል?
ያሬድ፦ ዓምና የነበረን ስብስብ ወጣት ተጨዋቾች የሚበዙበት ነበር፤ አሰልጣኙ በፀሎትም ክለቡን በጥሩ ብቃት ይመራው ስለነበርም ሊጉን ለመቀላቀል ችለናል።
ሊግ፦ የከፍተኛው ሊግ ውድድር ፈተናው ከባድ ነው?
ያሬድ፦ አዎን፤ ከመጀመሪያው ጨዋታ ጀምሮ ተቸግረንም ነበር፤ ወደ በኋላ ላይ ግን እኛ ጨዋታዎችን እያሸነፍን ስለተጓዝንና ከላይ ያለው ቡድን ደግሞ ነጥብን ስለጣለ ነገሮችን ቀላል አድርጎልን ሊጉን ለመቀላቀል ችለናል።
ሊግ፦ ከከፍተኛው ሊግና ከፕሪሚየር ሊጉ ከባዱ ውድድር የትኛው ነው?
ያሬድ፦ እስካሁን እንደተመለከትኩት ከባዱ ውድድር ፕሪምየር ሊግ ነው። ምክንያቱም እታችኛው ሊግ ላይ ስትጫወት ጥሩ ስኳድ ካለህ ግጥሚያዎች ቀላል ይሆኑልሃልና ወደምትፈልግበት ደረጃ ላይ መድረስ ትችላለህ።
ሊግ፦ በከፍተኛው ሊግ ተሳትፎአችሁ ለእናንተ ቡድን ፈታኝ የነበረው ክለብ ማን ነው?
ያሬድ፦ ነቀምት ከተማ ነዋ! ይህ ቡድን ፈታኝ የነበረውም ነጥቦችን የማይጥል ስለነበርና አቻ የሚወጣውም በጥቂት ጨዋታዎች ላይ ስለነበርም ነው።
ሊግ፦ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ዘንድሮ ሲጀመር ቅ/ጊዮርጊስ 7 ኢትዮጵያ መድን 1 የሚል ውጤት ተመዝግቧል፤ በወቅቱ የነበረህ ስሜት ምን ይመስላል?
ያሬድ፦ በኳስ እንዲህ ያሉ ሽንፈቶች አልፎ አልፎ የሚያጋጥሙ ቢሆንም የነበረው ስሜት ከባድና ያሳዘንም ነው። ያም ሆኖ ግን ከዛ ስሜት በፍጥነት በመውጣት ወደ አሸናፊነቱ ልናመራ ችለናልና ሀዘናችንን ወደ ደስታ እየቀየርነው ይገኛል። በእዚሁ አጋጣሚም ይህ ቡድንን በመምራት ለእዚህ ደረጃ እንዲበቃ እያደረገ የሚገኘውን አሰልጣኝ ገብረመድህን ሀይሌንም ላደንቀው እፈልጋለሁ።
ሊግ፦ ኢትዮጵያ መድን ሊጉን በሽንፈት ጀምሮ ነው ለጥሩ ውጤት በመብቃት ላይ የሚገኘው የክለቡ የውጤት ሚስጥር ምንድን ነው?
ያሬድ፦ የእኛ ቡድን የውጤት ሚስጥር ስራችንን በትጋት መስራታችንና ያለን አንድነትም ጥሩ መሆኑ ነው። ሌላው የአሰልጣኙ ልምምድን የማሰራት ብቃትና ለወጣት ተጨዋቾችም ያለው አመለካከት ጥሩ መሆኑም ነው ለስኬት ሊያበቃው የቻለው።
ሊግ፦ በውድድር ዘመኑ ምን ውጤትን ማምጣት አልማችሁ ነው የገባችሁት?
ያሬድ፦ የእኛ እልም ዋንጫና ዋንጫውን ማንሳት ነው። ከእዛ የሚያስቀረንም ምንም ነገርም የለም።
ሊግ፦ የ13 ሳምንታት የሊጉ ጨዋታ ተካሂዷል፤ ለእናንተ በጣም ያስደሰታችሁና ያስቆጫችሁ ጨዋታ የቱ ነው?
ያሬድ፦ በጣም ያስደሰተን ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናን ያሸነፍንበትና ወደ መሪነትም እንድንመጣ ያደረገን ጨዋታ ሲሆን ያዘንበት ደግሞ ብዙ ነገርን መስራት እየቻልን በቅ/ጊዮርጊስ በሰፊ ግብ የተሸነፍንበትን ጨዋታ ነው።
ሊግ፦ የቡድናችሁ ጠንካራ እና ክፍተት ጎኑ ምንድን ነው?
ያሬድ፦ ጠንካራው ጎናችን የቡድን መንፈሳችንና አንድነታችን ነው። ይህንን ማስቀጠልም እንፈልጋለን። ክፍተት ጎንን በተመለከተ ብዙም የለንም።
ሊግ፦ ለኢትዮጵያ መድን ምርጥ ግልጋሎትን እየሰጠህ ነው?
ያሬድ፦ አዎን፤ ከእዚህ በኋላም ምርጥ ግልጋሎቴን ለክለቤ እሰጣለሁ።
ሊግ፦ ለኢትዮጵያ መድን በእዚህ የውድድር ዘመን የቱ ክለብ ስጋት ይሆንበታል?
ያሬድ፦ ለእኛ ስጋትና ፈተና ሊሆንብን የሚችለው ክለብ ቅ/ጊዮርጊስ ነው። እነ ፋሲልም በቀጣይነት ሊሆኑብን ይችላሉና ዋናው ነገር ጠንክረን በመጓዝ የምንፈልገውን ውጤት ለማምጣት ጥረትን እናደርጋለን።
ሊግ፦ የቡድናችሁ አሰልጣኝ ገብረመድህን ሀይሌ በአንተ አንደበት እንዴት ይገለፃል?
ያሬድ፦ እሱ አንድ የያዘው ቡድንን በጥሩ መልኩ መስራት ይችላል። የተጨዋቾችን ብቃትም በሚገባ ያውቃልና በችሎታህ እንድትቀየርም ያደርግሃል።
ሊግ፦ የእግር ኳስ ተጨዋቾች ብዙ ጊዜ ከትምህርት ጋር አብረው አይጓዙም? አንተና ትምህርትስ?
ያሬድ፦ በ2010 ኢትዮጵያ መድን ስገባ ነው የ10ኛ ክፍል ትምህርቴን ያቆምኩት።
ሊግ፦ ወደ ኳታሩ የዓለም ዋንጫ እንሂድ፤ ስለ ውድድሩ ምን ትላለህ?
ያሬድ፦ ምርጥ ውድድር ነበር፤ አርጀንቲናም አስገራሚ ብቃቷን በማሳየት ሻምፒዮና ልትሆን ችላለች።
ሊግ፦ በውድድሩ የማን ደጋፊ ነበርክ? ምክንያትህስ?
ያሬድ፦ የፖርቹጋል ደጋፊ ነበርኩኝ ምክንያቱም ለሮናልዶ ልዩ ፍቅር ስላለኝና አድናቂው ስለሆንኩም ነው።
ሊግ፦ ዋንጫውን ግን የሊዮኔል ሜሲው አርጀንቲና አነሳች፤ ተናደድክ?
ያሬድ፦ ኸረ ደስ ነው ያለኝ፤ ምክንያቱም ድሉ ይገባታል።
ሊግ፦ ለአንተ የውድድሩ ምርጥ ቡድን ምርጡ ጨዋታና ተጨዋች ማን ነበር?
ያሬድ፦ ለእኔ ምርጡ ቡድን ብራዚል ስትሆን ምርጡ ተጨዋች ደግሞ ሊዮኔል ሜሲና ሌላው የአርጀንቲናው ተጨዋች ማካሊስተር ነው። ምርጡ ጨዋታ ደግሞ የፍፃሜው አርጀንቲና ከፈረንሳይ ያደረጉት ነው።
ሊግ፦ ከኳታሩ የዓለም ዋንጫ ምን ልንማር እንችላለን?
ያሬድ፦ የሜዳ ችግር አለብን፤ ያን ለማስተካከል ከቻልን የተጨዋቾቻችንን ኳሊቲ በማስተካከልና አቅሙም ስላለን ለትልቅ ደረጃ መብቃት እንችላለን።
ሊግ፦ ኢትዮጵያ መድን የሜዳ ችግር የለበትም?
ያሬድ፦ ልክ ነህ፤ ግን ጨዋታን እያደረገበት አይገኝም። የተመልካች ቦታን ሰርቶበት የደርሶ መልስ ጨዋታን ቢያደርግበት ጥሩ ነው። ተጠቃሚም ይሆንበታል።
ሊግ፦ ወደ ትዳር ዓለሙ ገብተሃል?
ያሬድ፦ አልገባውም።
ሊግ፦ የእረፍት ጊዜህን በምን እያሳለፍክ ነው?
ያሬድ፦ ብዙውን ጊዜዬን ከቤተሰቦቼና ከጓደኞቼ ጋር ነው የማሳልፈው። ከእዛ ውጪ ያለውን ደግሞ በግል ልምምድን በመስራትም ነው።
ሊግ፦ የአመጋገብ ምርጫህ ምንድን ነው?
ያሬድ፦ ፓስታ ነው የምወደው።
ሊግ፦ ዝምተኛ ወይንስ ተጨዋች?
ያሬድ፦ ዝምተኛ ነኝ።
ሊግ፦ ከቤተሰባችሁ ውስጥ ጨዋታ አዋቂው እና ቀልደኛው ማን ነው?
ያሬድ፦ አያቴ ተፈራ ቡልቲ ነዋ! እሱም ነው የሚያዝናናን።
ሊግ፦ በህይወት ዘመንህ በጣም የተደሰትክበት ቀንና የተከፋህበት?
ያሬድ፦ በጣም የተደሰትኩበት ቀን ዓምና ፕሪምየር ሊግ የገባንበትን ሲሆን የተከፋሁበት ቀን ደግሞ ዘንድሮ በቅ/ጊዮርጊስ በሰፊ ግብ የተሸነፍንበትን ነው።
ሊግ፦ የወደፊት ግብህ?
ያሬድ፦ የሀገሬን መለያ በማጥለቅ በሚገባ ማገልገል እፈልጋለሁ። ከእዛ ውጪም ለእኛ ለወጣት ተጨዋቾች አርአያ እንደሆነን እና ኩራት እንዲሰማን እንዳደረገንም አቡበከር ናስርም ወደ ውጪ በመውጣት መጫወትንም እፈልጋለሁ።
ሊግ፦ በመጨረሻ?
ያሬድ፦ በእግር ኳስ ተጨዋችነት በአጭር ጊዜ ውስጥ እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረሴ በቅድሚያ ፈጣሪዬን አመሰግናለሁ ።በመቀጠል ደግሞ ቤተሰቦቼን፣ ወደ ክለብ ተጨዋችነት እንዳመራ ብዙ ነገሮችን ያደረገልኝን አሰልጣኝ ይገዙ ሻንቆን እንደዚሁም ደግሞ በወጣት ተጨዋቾች ላይ እምነት ያለውን አሰልጣኝ ካሊድ መሀመድን፣ አሰልጣኝ ሀሰን በሽርን፣ አሰልጣኝ ፀጋዬ ወንድሙን፣ አሰልጣኝ በፀሎትን፣ አሰልጣኝ ያሬድ ቶሌራን፣ ከእዛ ውጪ ደግሞ የአሁኑ አሰልጣኜ ገብረመድህን ሀይሌ የመሰለፍ ዕድሉን እየሰጠኝ ስለሆነ ጭምር እሱንና ጓደኞቼን ለማመስገን እፈልጋለሁ።