Google search engine

“የሲቲ ካፑ ተሳትፏችን ውጤት ከማምጣት ባሻገር የያዝነውን እንቅስቃሴም የምናስቀጥልበት ነው” ፍቅረሰየሱስ ተ/ብርሃን (ኢት.ቡና)

በመሸሻ ወልዴ /G.BOYS/


የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ዛሬ ቅ/ጊዮርጊስ ከመከላከያ ባህር ዳር ከተማ ከወልቂጤ ከተማ በሚያደርጉት ጨዋታ ይጀመራል
የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን በገቢ ለማጠናከር ከዛ ውጪ ደግሞ ተወዳዳሪ ቡድኖች የራሳቸውን አቋም እንዲለኩበት ታስቦ የሚዘጋጀው ዓመታዊው የሲቲ ካፕ ዋንጫ ዘንድሮም ለ14ኛ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን ይኸው ውድድር ከዛሬ አንስቶም በድምቀት ይከናወናል፤ የሲቲ ካፑ ዋንጫ ሊጀመር የነበረው ባለፈው ሳምንት ቢሆንም በሀገሪቱ ከሚታየው የፀጥታ ችግር አኳያ ውድድሩ ለዛሬ ሊተላለፍ ችሏል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ዛሬ በይፋ ሲጀመርም የመጀመሪያ ተጋጣሚ ሆነው የሚቀርቡት ቡድኖች የምድብ አንድ ተፎካካሪ ክለቦች የሆኑት ተጋባዦቹ ባህር ዳር ከተማና ወልቂጤ ከተማ ሲሆኑ ጨዋታቸውንም ከ8 ሰዓት አንስቶ ያደርጋሉ፤ በቅዱስ ጊዮርጊስና በመከላከያ ክለቦች መካከል የሚካሄደው ሌላው የእዚህ ምድብ ተጠባቂ ጨዋታም ከቀኑ 10 ሰዓት አንስቶ ይከናወናል፡፡
የአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ዋንጫ የሌላው ምድብ ጨዋታም ነገ የሚቀጥል ሲሆን ከምድብ ሁለት በ8 ሰዓት ኢትዬ-ኤሌክትሪክ ከተጋባዡ ክለብ ወልዋሎ አዲግራት ጋር በ8 ሰዓት ጨዋታውን ሲያደርግ በ10 ሰዓት ደግሞ ኢትዮጵያ ቡና ከሌላው ተጋባዥ ቡድን ሰበታ ከተማ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ የሚጠበቅ ሆኗል፡፡
የአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ የዘንድሮ ውድድር ከፀጥታም ሆነ ከሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ውድድሩ በሰላም ተጀምሮ በሰላም የሚጠናቀቅበትን ነገር በሜዳ ላይ ለማሳየት የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንና ከየክለቦቹ የደጋፊ አስተባባሪዎች ጋር የቅድመ ዝግጅትን ውይይት ያደረጉ ሲሆን የእዚህ ዓመት ውድድርም በጥሩ መልኩ እንዲጠናቀቅም ሁሉም የስፖርት አፍቃሪም የየራሱን ድርሻ እንዲወጣም መልዕክት ሊተላለፍ ችሏል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ /ሲቲ/ ካፕ ዋንጫን ጅማሬ በማስመልከት ከተሳታፊ ክለባት አንድ አንድ ተጨዋቾች ጋር ቡድናቸው በሚያደርገው ጨዋታ ዙሪያና ስለ ዘንድሮ አጠቃላይ የውድድር ዘመን የዝግጅት ጊዜ ቆይታቸው ያናገርናቸው ሲሆን ተጨዋቾቹም የሰጡንን ምላሽ እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል፤ ተከታተሏቸው፡፡


የኢትዮጵያ ቡና የፕሪ ሲዝን ዝግጅትን በሚመለከት
“የኢትዮጵያ ቡናን የቅድመ ሲዝን ዝግጅት ዘግይቼ የተቀላቀልኩ ቢሆንም ወደ ቡድኑ ከገባሁበት ጊዜ አንስቶ ያለውን ልምምድ እንደተመለከትኩ በጣም ጥሩ የሚባልና ለየት ያለ ነው፤ የዝግጅቱ ሁኔታ ከኳስ ጋር የተያያዘና የማያሰለች ነው፤ ብዙ ጊዜ በዝግጅት ወቅት በአቅም ደረጃ ብዙ ጉልበቶችን የምታወጣበት ሁኔታ ቢኖርም የኢትዮጵያ ቡናው አዲሱ አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ በሚሰጠው ልምምድ ግን አቅምህን የሚጨርስ ስልጠና እየተሰጠን አይደለምና ይሄ ለእግር ኳሱ በጠቃሚነቱ ነው ልገልፅልህ የምወደው፤ የቡና ከኳስ ጋር የተያያዘው ልምምድ ድካም ያለው ቢሆንም ያለህን አቅምም በሚገባ አውጥተህ እንድትጫወትም ስለሚያደርግህ ደስ ብሎን ነው እየተለማመድን የምንገኘው”፡፡
ኢትዮጵያ ቡናን በመቀላቀልህ ምን አይነት ስሜት ተፈጥሮብሃል?
“ኢትዮጵያ ቡናዎች እኔን ፈልገውኝ እኔም ደግሞ እነሱን ፈልጌያቸው ክለቡን የተቀላቀልኩ ተጨዋች በመሆኔ ከዛ ውጪም ኢትዮጵያ ቡና ልጫወትበት የምመኘው አይነት ቡድን በመሆኑም አሁን ላይ ክለቡን ለመቀላቀል በመቻሌ ደስ የሚልና ጥሩ የሆነ ስሜት ነው እየተሰማኝ የሚገኘው”፡፡
ወደ ኢትዮጵያ ቡና በመምጣቱ ደስተኛ ስላደረገው ነገር
“ይሄ ምንም ሚስጥር የለውም፤ ወደ ኢትዮጵያ ቡና ለመምጣቴ ደስተኛ ያደረገኝ ነገር ቢኖር የቡድኑ የጨዋታ እንቅስቃሴ የሚስብና የምወደው አይነት በመሆኑ ነው”፡፡
ከኢትዮጵያ ቡና በፊት ለመከላከያ ፊርማውን አኑሮ ስለነበር
“የኢትዮጵያ ቡናን ከመቀላቀሌ በፊት ከሊጉ ወርዶ የነበረው መከላከያ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተወዳዳሪ ሆኖ ይቀጥላል የሚል ውሳኔ በመተላለፉ እኔ አስቀድሞ ልጫወትበት ከፈለግኩት ኢትዮጵያ ቡና ጋር በፊርማና በደመወዝ ክፍያ ሳልስማማ ቀርቼ በፕሪምየር ሊግ ደረጃ ለመጫወት ለተዘጋጀው መከላከያ ለመጫወት ወደ እነሱ አምርቼ ነበር፤ በኋላ ላይ ግን የፌዴሬሽኑ ውሳኔ ተሽሮ መከላከያዎች በታችኛው ሊግ ወርዳችሁ ተጫወቱ የሚል ህግ ሲወስንባቸው እኔ ደግሞ በእዛ ህግ ሳልስማማ ቀረሁና ወደ ኢትዮጵያ ቡና አመራሁ”፡፡
በኢትዮጵያ ቡና የተጨዋችነት ቆይታው ምን አይነት የውድድር ጊዜን እንደሚያሳልፍ
እና ኢትዮጵያ ቡና በርካታ ደጋፊ የያዘ ክለብ ከመሆኑ አንፃር በመጫወትህ ላይ ጫና ወይንም ደግሞ ተፅዕኖ ይፈጠርብኛል ብለህ ትሰጋለህ?
“በፍፁም፤ ለኢትዮጵያ ቡና ለመጫወት ወደ ቡድኑ ስመጣ አንዳችምም፤ ምንም አይነትም የስጋት ስሜት ኖሮብኝ አይደለም፤ ለእዚህም በምክንያትነት ማስቀመጥ የምፈልገው ነገር ይሄ ክለብ የአንተን ማንነትና ችሎታህንም ጭምር በጣም የምታሳይበት ስለሚሆንልህ ነው፤ በእግር ኳስ ጨዋታ እንደውም እስከዛሬ በእንዲህ ያለ አይነት ቡድን አለመጫወቴም ነው ለታላቅ ስፍራ ላይ እንዳልደርስ ያደረገኝ፤ ይሄን ለማለት የቻልኩት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ለትልልቅ ቡድኖች መጫወት ከፍተኛ ጥቅም ስላለው ነው፤ ከዚህ በፊት ኳሱን የሌላ ቡድን ወይንም ደግሞ ብዙም ደጋፊ የሌለበት ቡድን ውስጥ ተጨዋች ሆነህ ስታሳልፍ ለብሄራዊ ቡድን የምትጠራበት ሁኔታ ቢኖርም ከፈለጉህ ሊዘሉ እና ላይጠሩ ይችላሉ፤ ይሄ እኔን ገጥሞኛል፤ እንደ ቡና ባለህ ክለብ ውስጥ ግን በሌላ ቡድን ውስጥ ያለህን ትንሽ ነገር በሜዳ ላይ ካሳየህ የምትፈልገውን ነገር ማግኘት ትችላለህና ቡና በመምጣቴ ከመደሰት ውጪ የምሰጋበት ምንም ነገር የለም”፡፡
የኢትዮጵያ ቡናን የተጨዋቾች ስብስብ በተመለከተ
“ስለ ኢትዮጵያ ቡና የተጨዋቾች ስብስብ አሁን ላይ ሆኜ ብዙ ነገርን ማለት አልፈልግም፤ ክለቡ እነዚህን ተጨዋቾች ለእኔ ይመጥናሉ፤ ከአጨዋወታችንም ጋር አብረው ይሄዳሉ በሚልም ነው እምነት ጥሎባቸው ያስመጣቸውና የክለቡን አመለካከት ከመቀጠል ውጪ ሌላ ምንም የምለው ነገር የለኝም”፡፡
በኢትዮጵያ ቡና ክለብ ውስጥ በቋሚ ተጨዋችነት ለመሰለፍ ጠንካራ ፍልሚያ ይጠበቅብኛል ብለህ ታስባለህ?
“እንደዛ ለማለት እንኳን ይከብደኛል፤ ያም ቢሆን ግን ቡናን የተቀላቀልኩት ዘግይቼና የፕሪ ሲዝን ልምምድን ከጀመሩ በኋላ በመሆኑ እንደዚሁም ደግሞ የክለቡም አዲስ ተጨዋች ስለሆንኩ ከሰራሁት እንቅስቃሴ አንፃር መጀመሪያ አካባቢ ለቡድኑ ላልጫወትና ልቀመጥ እችል ይሆናል፤ በሂደት ቆይታዬ ግን ስራዬን ጠንክሬ የምሰራ ተጨዋች ስለሆንኩ በቡና ውስጥ የተሻለ ብቃት ላይ ተገኝቼ ክለቡን በቋሚ ተሰላፊነት እንደማገለግል አስባለሁ”፡፡
ኢትዮጵያ ቡና በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ስለሚያደርገው የውድድር ተሳትፎና ሰበታ ከተማን ስለሚገጥምበት የመጀመሪያው ጨዋታ
“የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ የዘንድሮው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ የሚያደርገው የውድድር ተሳትፎው የተወሰኑ ተጨዋቾቹ ወደ ብሄራዊ ቡድን ያመሩበት ከመሆኑ አኳያና በእዚህ አመትም በፕሪምየር ሊጉ ላይ ለሚኖሩት ጨዋታዎቹ ራሱን በሚገባ የሚያዘጋጅበት እንዲሁም ደግሞ ሌሎቹን ተጨዋቾችም የሚያይበት ውድድር ስለሆነ በእዚህ ውድድር ላይ ጥሩ ውጤት ለማምጣትና በፕሪ ሲዝኑ ላይም እየተገበረ ያለውን የቡድኑን የጨዋታ እንቅስቃሴ ለማስቀጠልም በሚገባ የተዘጋጀበት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ቡና ከሰበታ ከተማ ጋር ስለሚያደርገው የመጀመሪያ ቀን ጨዋታውም ግጥሚያውን በድል አድራጊነት ያጠናቅቃል”፡፡
የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ከልምምድ ውጪ ስለሚሰጣቸው የሀሳብ መመሪያ
“የኢትዮጵያ ቡናው አዲሱ አሰልጣኝ በሜዳ ውስጥ ከልምምድ ውጪ ምን ማድረግ እንደሚገባን የሚሰጠን መመሪያ በጣም ጥሩ ነው፤ የእሱን ንግግር ካዳመጥኩ በኋላም ከሀሳቡ በመነሳት ወደ ክለቡ አሁን ላይ መምጣቱ እንደውም በጣም ዘግይቷል ብዬም ነው እንዳስብ ያደረገኝ፤ ካሳዬ ቀደም ብሎና በፊት መጥቶ ቢሆን ኖሮ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ለውጥም ብዙ ነገሮችን መስራት የሚችል ያህልም ይሰማኛል”፡፡
የኢትዮጵያ ቡናን ደጋፊዎቹ ባሉበት ተቃራኒ ሆነህ ገጥመሃል፤ አሁን ደግሞ በእነሱ ፊት ታጅበህ ልትጫወት ተዘጋጅተሃል፤ ስሜቱ ምን ሊሆን ይችላል?
“የኢትዮጵያ ቡናን በደጋፊዎቹ ፊት የተቃራኒ ቡድን ተጨዋች ሆኜ ስገጥም ሁሌም ነው ከፍተኛ እና የተለየ ያህል የደስታ ስሜት የሚሰማኝ፤ የእነሱ ድጋፍ ለየት የሚል ነው፤ ክለቡ ምርጥ የሚባሉ ደጋፊዎች አሉት፤ ሲዘምሩና ሲጨፍሩ አንተን በጣም ያነቃቁሃል፤ አንዳንዴ እንደውም እነሱን ለመመልከት ጭምር ወደ ሜዳ የምንገባበት ጊዜም ነበርና አሁን ላይ ደግሞ በእነሱ ፊት ለመጫወት በመዘጋጀቴ በጣም ደስተኛ ነኝ”፡፡
በኢትዮጵያ ቡና ክለብ ውስጥ በምን መልኩ ለመጫወት እንደተዘጋጀ እና በመጨረሻም ምን መልዕክቱን ማስተላለፍ እንደፈለገ
“የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ውስጥ ዘንድሮ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ መልኩ እና ብቃቴ ለመቅረብ በጣም ዝግጁ ነኝ፤ ከዛ ውጪም ማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክት ቡና አሁን ላይ የያዘው አጨዋወት ለየት ያለና ወጣ ያለ በመሆኑ ከዛ ባሻገር ደግሞ ይህ እንቅስቃሴ ወደፊትም አዋጭ ስለሆነ ደጋፊዎቻችን ሁሉን ነገር በትዕግስት ጠብቀው የውጤት ፍሬውን እንዲያዩ ነው የምፈልገው”፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this: