በመሸሻ ወልዴ /ጂቦይስ/
የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከሰበታ ከተማ በማገናኘት ነገ ይጠናቀቃል
የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለ14ኛ ጊዜ ያዘጋጀው የከተማው የዋንጫ ውድድር ነገበድምቀት ይጠናቀቃል፡፡
የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን በገቢ ለማጠናከር እና ክለቦችም የራሳቸውን አቋም እንዲለኩበት ታስቦ የተካሄደው ይኸው ውድድር ነገ ሲጠናቀቅም ሰበታ ከተማን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ለፍፃሜ የሚያገናኝ ሲሆን ሁለቱ ቡድኖች ለፍፃሜ ደረሱትም ሰበታ ከተማ መከላከያን 3ለ1 ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ኢትዮጵያ ቡናን 2ለ0 በማሸነፍ ነው፤ የደረጃው ጨዋታ ደግሞ ዛሬ ኢትዮጵያ ቡናን ከመከላከያ ጋር በ10 ሰዓት ያገናኛል፡፡
የአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ የፍፃሜ ጨዋታን አስመልክተን ከሰበታ ከተማው ታደለ መንገሻ እና ከቅ/ጊዮርጊሱ አቤል ያለው ጋር ቆይታን ያደረግን ሲሆን ተጨዋቾቹም ምላሻቸውን በሚከተለው መልኩ ሰጥተውናል፡፡
ሊግ፡- ሰበታ ከተማ መከላከያን በማሸነፍ ነገ ለሚጠናቀቀው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ አልፏል፤ ጨዋታችሁ ምን መልክ ነበረው? በድሉስ ምን ተሰማህ?
ታደለ፡- የመከላከያ እግር ኳስ ክለብን በግማሽ ፍፃሜው ድል ያደረግንበት ጨዋታ በሁለታችንም መካከል ጥሩ ፉክክር የተደረገበት ሲሆን በመጀመሪያው አጋማሽ እኛ አቻ በመለያየት በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር ጨዋታውን በድል አድራጊነት ልናጠናቅቅ ችለናል፤ በእዚህ ጨዋታም ቡድናችን ግጥሚያውን ለማሸነፍ የረዳው ከአሰልጣኛችን የተሰጠንን የታክቲክ ትግበራ በሚገባ ልንተገብር በመቻላችን ነውና ባገኘነው ድል በጣም ተደስተናል፡፡
ሊግ፡- መከላከያን ያሸነፋችሁበት ጨዋታ ውጤት ይገባችኋል?
ታደለ፡- አዎን፤ የጨዋታ ውጤት ይገባናል፤ ምክንያቱም ወደዚህ ውድድር ስንመጣ ግጥሚያዎቹ ለዘንድሮ የፕሪምየር ሊግ ውድድር ተሳትፎአችን አቋማችንን በሚገባ የምንለካበት ነው ብለን ስላሰብን እና በደንብም ስለተዘጋጀንበት ነው አሸናፊ ለመሆን የቻልነው፤ በጨዋታዎቹ ሁሉም ጠንካራ እንቅስቃሴን በማድረግም ነው ለፍፃሜው ጨዋታ ልንቀርብ የቻልነው፡፡ በእግር ኳስ ጨዋታ ትልቁ ነገር ሁለቱንም አይነት መከላከልንም ማጥቃትንም ተግባራዊ ማድረግ አለብህና የእኛ ቡድን አጨዋወቱን ሁሉ ወደፊት በማድረግም ነው የግጥሚያው አስፈሪ ሊሆን የቻለው፡፡
ሊግ፡- መከላከያን በግማሽ ፍፃሜው እንዴት አገኛችሁት?
ታደለ፡- መከላከይ ጥሩ ቡድን ነው፤ ለእዚህም ነው በምድቡ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ እስከ ግማሽ ፍፃሜው ደረጃ ሊመጣ የቻለውና ጥሩ ቡድንን ነው ያሸነፍነው፡፡
ሊግ፡- የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ተሳትፎአችሁ ላይ ክለባችሁ በእንቅስቃሴ ደረጃ ከጨዋታ ወደ ጨዋታ መሻሻል አለው ወይንስ ተመሳሳይ አጨዋወት ነው እየተከተለ የሚገኘው?
ታደለ፡- የሰበታ ከተማ እግር ኳስ ክለብ የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ተሳትፎ ላይ እንደተመለከታችሁት ከጨዋታ ወደ ጨዋታ መሻሻልን እያሳየ ነው የሚገኘው፡፡ ለእዛ ደግሞ ከአሰልጣኛችን ስልጠና ባሻገርጥሩም የአካል ብቃት ልምምድ እየሰራን ናውና ከዚህም በላይ እንሻሻላለን፡፡
ሊግ፡- የሰበታ ከተማ የፍፃሜ ተጋጣሚ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወይንም ደግሞ ኢትዮጵያ ቡና ይሆናል፤ በእሁዱ መዝጊያ ጨዋታ ማን የውድድሩ አሸናፊ ይሆናል?
ታደለ፡- የእሁዱ የፍፃሜ ጨዋታ ላይ እኛ ቅዱስ ጊዮርጊስም ሆነ ኢትዮጵያ ቡና ይድረሱን ለተጋጣሚዎቻችን በቅድሚያ ክብር ነው የምንሰጠው፡፡ እኛ ደግሞ የተሻለ ነገር ሰርተን በመምጣት ዋንጫውን እንደምናነሳ ከፈጣሪ ጋር ተስፋ አለኝ፡፡/ያነጋገርነው ሐሙስ ጠዋት ነበር/፡፡
ሊግ፡- ከቅዱስ ጊዮርጊስ ማንም ባልጠበቀ ሁኔታ ለቀህ ሰበታ ከተማን ነው የተቀላቀልከው፤ የወጣህበት ምክንያት ምን ነበር?
ታደለ፡- ቅ/ጊዮርጊስ የሃገሪቱ ትልቅ እና ውጤታማ ቡድን ነው፡፡ ከእነሱ ጋር በነበረኝ ቆይታም ደስተኛ ነበርኩ በኋላ ላይ ግን ውሌን እንዳጠናቀቅኩ በእነሱ ስላልተፈልግኩ ከክለቡ ጋር ባላሰብኩት እና ባልጠበቅኩት ሁኔታ ተለያይቻለው፤ አሁን ላይ ደግሞ በአዲሱ ቡድኔ ደስተኛ ሆኜ ስራዬን እየሰራሁ ነው የምገኘው፡፡
ሊግ፡- ከቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ጋር መለያየትህ ቆጭቶሃል?
ታደለ፡- መቆጨት ሳይሆን ከክለቡ ጋር መለያየቴን ለበጎ ነው ብዬ ነው የወሰድኩት፡፡
ሊግ፡- በሰበታ ከተማ ዘንድሮ ከአንተ ምን ይጠበቅ?
ታደለ፡- ብዙ ነገሮች በአዲሱ ቡድኔ ውስጥ ይጠበቅብኛል፤ ምክንያቱም ከጉዳቶች የተነሳ ከጌም ርቄ ነበር፤ ጠንክሬ ሰርቼ ክለቤንም የብሄራዊ ቡድናችንንም ማገልገል እፈልጋለሁ፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ኮትዲቩዋርን አሸነፈ?
ታደለ፡-በውጤቱ በጣም ነው የተደሰትኩት፤ ይሄ ጨዋታም የትኛውንም ትልቅ ቡድን ስታካብድ ከገባህ ማሸነፍ እንደምትችል ትምህርት የሰጠ ግጥሚያ በመሆኑ አሰልጣኞቹንም ተጨዋቾቹንምበእዚህ አጋጣሚ ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡
ሊግ፡- የሰበታ ከተማ የተጨዋቾች ስብስብ ምን ይመስላል?
ታደለ፡- በጣም የሚገርም ስብስብ ነው ያለን፤ እኔ እንደውም ራሴን እድለኛ አድርጌም ነው የምቆጥረው፤ ለምን ሲኒየር የሆኑ ተጨዋቾች ጋር ነው የተገናኘሁት፡፡ አሰልጣኙ የሚሰጠው እለታዊ ልምምድም የተለያየ ስለሆነ በጣም ደስ ይላል፤ እኔም ደስተኛ ሆኜ ነው ልምምዴን እየሰራሁ ያለሁት፡፡
ሊግ፡- የሰበታ ከተማ ከመከላከያ ጋር ባደረገው ጨዋታ የግጥሚያው ኮከብ ተብለህ ተሸልመሃል፤ ምን ተሰማህ?
ታደለ፡- የሰበታ ከተማ ከመከላከያ ባደረገው ጨዋታ አንድ ተጨዋች ኮከብ ተብሎ መሸለም ስላለበት ተሸለምኩ እንጂ ሙሉ ቡድኑ ነው ለእኔ ኮከብ የነበረው፤ በእዚህ ደስተኛ ሆኛለሁ፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ…?
ታደለ፡- ሰበታ ከተማ በሲቲ ካፕ ላይ እያደረገ ባለው ጥሩ እንቅስቃሴ ደስተኛ ነኝ፤ እስከፍፃሜው በመጓዛችንም የቡድኑን አሰልጣኞች እና እናን ሲደግፉን የነበሩትና ደጋፊዎች ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡