በመሸሻ ወልዴ /G.BOYS/
የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ እና የአሸናፊዎች አሸናፊ የዋንጫ ባለቤት በመሆን ያለፈውን ዓመት የውድድር ዘመን በስኬት ያሳለፈው ፋሲል ከነማ የዘንድሮውን የፕሪምየር ሊግ ውድድር ዋንጫ ማንሳት መቻል ደግሞ ዋንኛ ፍላጎቱና እልሙ እንደሆነ የቡድኑ የአማካይ ስፍራ ተጨዋች በዛብህ መላዮ ለሊግ ስፖርት ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ተሳትፎው ላይ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴም ሆነ በውጤታማነት ጠንካራ ቡድንን ካለፈው ዓመት አንስቶ በመገንባት ዓምና ለጥቂት የሊጉን ዋንጫ ያጣው ፋሲል ከነማ በእዚህ ዓመት ባደረጋቸው የእስካሁን ጨዋታዎች የሊጉን መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስን ተከትሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን ክለቡ ነገ እሁድ በሜዳው ፋሲለደስ ስታድየም እና በደጋፊዎቹ ፊት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ ማሸነፍ ከቻለ የሊጉን መሪነት የሚጨብጥበት ዕድል ይፈጠርለታል፡፡
የሁለቱን ቡድኖች ጨዋታ አስመልክቶም ጥያቄ የቀረበለት በዛብህ መላዮም “የእሁዱ ተጋጣሚያችን ቅዱስ ጊዮርጊስ አሁን ላይ ተጠናክሮ መጥቷል፤ ያም ሆኖ ግን ከእነሱ ጋር የሚኖረንን ጨዋታ አሸንፈናቸው መሪነቱን የምንነጥቃቸው ይሆናል” ሲልም ምላሹን ሰጥቷል፡፡
የፋሲል ከነማው በዛብህ ከዛ ውጪም ዘንድሮ “የሊጉ ሻምፒዮና የምንሆነውም እኛ ነንም” ሲል ይናገራል፡፡ ከተጨዋቹ ጋር የነበረን አጠቃላይ ቆይታም በሚከተለው መልኩ ቀርቧል፤ እንደሚከተለውም ተስተናግዷል፡፡
ሊግ፡- በፕሪምየር ሊጉ ዘንድሮ ይዛችሁት የቀረባችሁት አቋም ከአምናው የተሻለ ነው ወይንስ በተቃራኒው?
በዛብህ፡- ለእኔ በጣም የተሻለ ነው እንጂ፤ ምክንያቱም በእዚህ ሰዓት ላይ ባሠመመመመለፈው ዓመት በብዙ ነጥብ ነበር በመሪው ክለብ መቐለ 70 እንደርታ ተበልጠን የነበረው፡፡ አሁን ላይ ግን የእሁዱን ጨዋታ ማሸነፍ ከቻልን መሪ ልንሆን የምንችልበት እድሉ በእጃችን ውስጥ ስላለ ያንን ስኬትም እውን እናደርገዋለን፡፡
ሊግ፡- በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮ ተሳትፏችሁ የትኛው ጨዋታ እናንተን አስቆጭቷችኋል?
በዛብህ፡- የተቆጨንበት ጨዋታ ከሰበታ ከተማ ጋር ያደረግነው ነው፤ ይሄን ፍልሚያም አሸነፍን ብለን ባጠናቀቅንበት ሰአት እና 3-1ም እየመራን በነበርንበት ሰአት በጭማሪዎቹ ደቂቃዎች ላይ ነው ተዘናግተን በተቆጠሩብን 2 ግቦች አቻ ለመለያየት የቻልነውና ያ ጨዋታ ሶስት ነጥብ እንዳናገኝ ያደረገን ስለነበር ግጥሚያው ፈፅሞ የሚረሳኝ አይደለም፡፡
ሊግ፡- በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ማንሳቱ ላይ ዘንድሮ ለእናንተ ከባድ እና ስጋት ሊሆንባችሁ የሚችለው ክለብ ማን ነው?
በዛብህ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊጉን እየመራ እና የአሁን ሰአት ላይም ደግሞ በወቅታዊ አቋሙ ከጨዋታ ወደ ጨዋታ ሲያመራ ራሱን በጣም እያጠናከረ የመጣበት ሁኔታ ስላለ እና ጥሩም ስለሆነ ዋንኞቹ ስጋታችን እነሱ ናቸው፤ የዓምናው ሻምፒዮናም መቐለ 70 እንደርታም ጠንካራ ተፎካካሪዎቻችን ናቸው፡፡
ሊግ፡- ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የምታደርጉትን የእሁዱ ጨዋታ በጎንደር ፋሲለደስ ስቴድየም በሜዳችሁ እና በደጋፊዎቻችሁ ፊት ከማከናወናችሁ አኳያ ይሄ ጨዋታ ለእናንተ የተለየ እና ትርጉም ያለው ጨዋታ ይሆናል ማለት ይቻላል? ምንስ ውጤት ይመዘገብበታል?
በዛብህ፡- ከቅዱስ ጊዮርጊስ የሚኖረን የነገው የእሁድ ጨዋታ ለእኛ የተለየ ነው ብዬ ባላስብም ይህን ጨዋታ ማሸነፍ መቻል ግን በመሪነቱ ስፍራ ላይ የሚያስቀምጠን ስለሆነ ያንን በተግባር ማሳየትን እንፈልጋለን፤ ጨዋታውን ከተሸነፍን ግን መሪው ቡድን በነጥብ እየራቀ እንዲጓዝ እና መሪነቱንም እንዲያስጠብቅ እድልን ስለምንፈጥርለት ይሄን ጨዋታ ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ ተጫውተን 3 ነጥብን ይዘን እንደምንወጣ እርግጠኛ ነኝ፡፡
ሊግ፡- በቅዱስ ጊዮርጊሶች በኩል ፋሲል ከነማን አሸንፈን መሪነቱን እናጠናክራለን እያሉ ነው?
በዛብህ፡- እኛ ደግሞ ሊጉ ከተጀመረ አንስቶ እዚሁ የራሳችን ሜዳ ላይ ነጥብ ተወስዶብን ስለማያውቅ ግጥሚያውን እናሸንፋለን እንላለን፡፡
ሊግ፡- ፋሲል ከነማን በተጨዋቾች ስብስቡ ከአምናው አንፃር ስትመዝነው በምን መልኩ ትገልፀዋለህ?
በዛብህ፡- በስብስባችን ደረጃ የአሰልጣኝ ቅያሪ ካልሆነ በስተቀር የዓምናው ስኳድ ነው ዘንድሮም ያለን፤ ዓምና ይሄን ስብስብም ይዘን ነው በ10 ነጥብ እና በ11 ነጥብ ነበር በመሪው ክለብ የምንበለጠው፤ አሁን ላይ ግን በ1 ነጥብ ብቻ ተበልጠን እየተከተልንና የእሁዱን ጨዋታ ካሸነፍን ደግሞ መሪ ልንሆን ስለምንችል ዘንድሮም በተጨዋቾች ስብስባችን ጥሩ ቡድን ነው ያለን፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ከሜዳ ውጪ ማሸነፍ መቻል ከባድ ነው የሚል አባባል እየሰማን ይገኛል፤ ወጥቶ ማሸነፍ የእውነት ከባድ ነው?
በዛብህ፡- ከሜዳ ውጪ ማሸነፍ መቻል ሁሌ ሳይሆን አንዳንዴ ይከብዳል፤ እኛ ለምሳሌ ጅማ ላይ ሄደን ስንጫወት የእነሱ ደጋፊ የእኛ እስኪመስለን ድረስ ነው ጥሩ ስንጫወት የነበረው፡፡ ኳስን በመቆጣጠርና ፖሰስ በማድረግም ነበር በልጠን የተጫወትነው፤ ያም ሆኖ ግን እድለኛ ስላልነበረን ሳናሸንፍ ቀርተናል፡፡ ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር በነበረን ጨዋታ ደግሞ ግጥሚያው በጣም ከባድ የሚባል ቢሆንም የሜዳችን ውጪ ጨዋታን ነው አሸንፈን የመጣነውናአንዳንዴ ነገሮች እንደጠበቅከው አይሆንልህም፡፡ የእኛ ቡድን ደግሞ በሜዳውም ሆነከሜዳውም ውጭ ሲጫወት ግብ ለማግባት እና ለማሸነፍ ነው የሚጫወተው፡፡ አንድ ግብ ብቻ አስቆጥረን ለማሸነፍ ሳይሆን ተጨማሪም ግብም ለማስቆጠርም ነው የምንጫወተው፤አንድአንዴ እየመራን ሁሉ ውጤቱን እንደሌሎች ቡድኖች አስጠብቅን ለመጫወትም አይደለም ሜዳ ላይ የምንቆየው ተጨማሪ ግቦችም ለማግባትም ነው የምንጫወተውና ከዚህ በኋላምበሚኖሩን ጨዋታዎች የሜዳ ውጪ ጨዋታን ማሸነፍ ጀምረናልና ይሄንን ነው ማስቀጠል የምንፈልገው፡፡
ሊግ፡- ብዙ ቡድኖች ከሜዳ ውጪ ማሸነፍ መቻል ከባድ ነው የሚሉት ነገር ምንን ተንተርሰው ነው?
በዛብህ፡- ለእኔ እንደሚመስለኝ አንድአንዴ ኳስ የሚጫወቱ ቡድኖች አሉ፤ ብዙ ጊዜ እነዚህ ቡድኖች ጥሩ የሚጫወቱትና ውጤታማ የሚሆኑት የሚጫወቱበት ሜዳ የተመቻቸው ሲሆን ነው፤ አሁን እንደ ባህርዳር ያለውን የእኛው ቡድን ሜዳ ፋሲለደስ ስቴድየምን የሐዋሳ ስቴድየምን እና የአዲስ አበባ ስቴድየምን ሜዳዎች ብትወስድ ለጨዋታ ምቹ ነው፤ እነሱ አሁን ወደ ክልል ወጥተው ወደ ሆሳዕና ሜዳና መሰል ሜዳዎች ላይ ሄደህ ውጤት ይዤ እመጣለሁ ማለት በጣም ከባድ ነውና ከሜዳ አንፃር ነው ወደ ክልል ተጉዞ ማሸነፍ ክብደትነቱ፡፡
ሊግ፡- የፋሲል ከነማ ክለብ እና ደጋፊው አሁን ላይ ዋንጫ የተራበ ይመስላል፤ ይሄ አባባል ያስማማሃል….? ዘንድሮስ ይሄ ጥማቱን የምታስታግሱለት ይመስላቹሃል?
በዛብህ፡- አዎን፤ የጥሎ ማለፉንና የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን ቡድናችን አምና አንስቷል፤ አሁን ላይ ደግሞ ቡድናችንም ሆነ ደጋፊዎቻችን ሊያገኙት የሚፈልጉት ዋንጫ የፕሪምየር ሊጉን ነውና ከሁሉም በላይ ደግሞም የቡድናችን እያንዳንዱም ተጨዋች የእዚህ ታሪካዊ ድል ባለቤት መሆንን አጥብቆ ስለሚፈልግ፤ አብዛኞቹ ተጨዋቾችም ይህንን ዋንጫም ከዚህ ቀደም ያላገኙ ስለሆኑም ዘንድሮ ይህንን ህልም ለቡድኑም ሆነ ለእኛ የምናሳካው ይመስለኛል፡፡
ሊግ፡- የፋሲል ከነማ የተጨዋቾች ስብስብ ውስጥ እንደ እነ ሽመክት ጉጉሳ እና ጀማል ጣሰውን የመሳሰሉ ተጨዋቾች የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ከማንሳታቸው ጋር ተያይዞ ጣዕሙን ያውቁታል፤ አንተን ጨምሮ ስለዚህ የዋንጫ ድል ጣዕም ያላዩ ተጨዋቾችስ ይሄን ሲያስቡ ምን ይላሉ?
በዛብህ፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ በቆየሁባቸው ጊዜያቶች ከወላይታ ድቻ እና ከፋሲል ከነማ ጋር ሁለት ጊዜ የጥሎ ማለፍ ዋንጫን እንደዚሁም ደግሞ ከፋሲል ከነማ ጋር አንድ ጊዜ የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን ድል ማጣጣም መቻሌዋናው የምፈልገው እና እንዲህ ያሉ ድሎችንም ማሳካት መቻል ልዩ ትርጉም የነበረው ነውና በእዚህ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ በኳስ ህይወቴ አሁን ያላሳካሁት ድል ደግሞ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ማንሳት መቻልነው፤ ይሄን አጋጣሚም ወደፊት ላላገኘው ስለምችል ዘንድሮ ይሄን ድል በአግባቡ ለመጠቀምና ያለውንም የደስታ ጣዕም ለማወቅም በጣም የጓጓሁበት ሁኔታ ስላለ ለእዚያ እንደ ሁሉምየቡድናችን ተጨዋቾች እኔም ከፍተኛ መስዋዕትነትን ለመክፈል እየተዘጋጀው ነው የምገኘው፡፡
ሊግ፡- እንደ ፋሲል ከነማ ክለብ ተጨዋችነትህ ይሄ ነገር ይጎድለናል፤ ልናስተካክለውም ይገባናል የምትለው ነገር ምንድነው?
በዛብህ፡- በውድድሩ ቆይታችን ያንን ያህል ብዙ ይጎለናል የምለው ነገር ባይኖርም አልፎ አልፎ ግን ትንሽ በአንድአንድ ጨዋታዎቻችን ላይ በጉዳት ልጆቻችንን የምናጣበት ሁኔታ አለና የሁለተኛው ዘር ላይ አሰልጣኙ በዚህ ዙሪያ የሚያውቀው ነገር ስላለ ያንን ያስተካክለዋል ብዬ አስባለሁ፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮ ፉክክር ላይ ለአንተ በችሎታው የተለየው ተጨዋች ማን ነው?
በዛብህ፡- በዋናነት የእኛው ሙጂብ ቃሲም ነዋ! ምክንያቱም ይሄ ተጨዋች ከዚህ ቀደም በነበሩት ዓመታት በተከላካይ ስፍራ ላይ ሆኖና ጨዋታን ጀምሮ በአጥቂነት እየተሳካለት ያለ በመሆኑ ነው፤ ተጨዋቹ ካለፉት አመታት አንስቶም ጎል እያስቆጠረ ነው፤ ዘንድሮም የፕሪምየር ሊጉን የኮከብ ግብ አግቢነት እየመራም ነውና እሱ ለየት ይላል፤ ሌላው ልጠቅሰው የምፈልገው ተጨዋች ደግሞ ምንም እንኳን ቡድናችንን ዘንድሮ ለቀቀ እንጂ የአሁን ሰአት ላይ ለባህር ዳር ከተማ በመጫወት ቡድኑን እየጠቀመ የሚገኘው ፍፁም ዓለሙ ብቃቱን በጣም በማሻሻል ላይ ያለ የተለየ ተጨዋች ሆኖብኛልና እሱን ሳልጠቅሰው የማላልፈው ተጨዋች ነው፡፡
ሊግ፡- በዛብህ ባለው ወቅታዊ አቋሙ እንዴት ይገለፃል? የተለየ ተጨዋችስ ሆነህ ቀርበሃል?
በዛብህ፡- የወላይታ ድቻ ክለብ ውስጥ በነበርኩ ሰአት የአንደኛው ዙር ውድድርን ብዙ ጊዜ በጉዳት አሳልፍ ስለነበር ጨርሼ አላውቅም፤ አምናም በዚህ ሰአት ለፋሲል ከነማ ስጫወት በጉዳት የተነሳ እየተጫወትኩ አልነበረም፤ ዘንድሮ ግን እስከዚህ ሰአት ድረስ ለቡድኔ ጥሩ እየተጫወትኩ ነው ያለሁትና ይሄ ያለሁበትን ጥሩ አቋሜን ይገልፅልኛል፤ የእግር ኳስ ተጨዋች ስትሆን ጉዳት በሚያጋጥምህ ሰዓት ብዙ ነገሮችን ታጣለህ እና አሁን ግን እየተጫወትኩ ከመሆኔ አኳያና ቡድኔንም በደንብ እያገለገልኩት ስለሆነ ለእኔ ከወቅታዊ አቋሜ አንፃር ይሄ ዓመት ጥሩ እየሆነልኝ ነው፡፡
ሊግ፡- የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች እናንተን ዘንድሮ ሲያገኛችሁም ሆነ በሌሎች ሁኔታዎች ላይ ስትመለከቷቸው ያላቸው ስሜት ምን ይመስላል…. እነሱ እንዴትስ ነው ሊገለፁ የሚችሉት?
በዛብህ፡- የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች የተለዩ እና ሁሉንም ነገራቸውንም ለቡድናቸው የሰጡ ስለመሆናው እኔ ብቻ ስልሆን የሌላ ቡድን ደጋፊዎችም ሆኑ በተለይ ደግም የእኔ የቅርብ ጓደኛ የሆኑ የሌላ ቡድን ተጨዋቾች በተደጋጋሚ የሚገልጿቸው ነገሮች አሉና የእውነቴን ነው የምልህ እንደ እነሱ አይነት ደጋፊዎችን ተመልክቼ አላውቅምና ለሚሰጡን ድጋፍ ሁሉ በጣሙን ሊመሰገኑ ይገባል፤ በእርግጥ አልፎ አልፎ አንድ አንድ አስቸጋሪ ደጋፊም በመሃል ይኖራል፤ ያም ሆኖ ግን ሁሌም ማዕከል ማድረግ ያለብን ብዙዎችን ስለሆነም የፋሲል ከነማ ደጋፊ ራሱን ያለስስት ለቡድኑ ሰጥቶ የሚገደፍ ነውና ለእኔ ኳስን ለይተው ከማወቅ አንፃርም ሁሌም የተለዩ ናቸው፡፡ ዘንድሮ እኛን ሲያገኙንም ዋንጫውን አጥብቀው እንደሚፈልጉትም ይነግሩናልና ያንን ህልማቸውንም ልናሳካላቸው ተዘጋጅተናል፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ በብዙ አሠልጣኞች ሰልጥነሃል፤ ለአንተ ምርጡ እና የተለየው አሰልጣኝ ማን ነው? ከእነ ምክንያቱ ምላሽ ብትሰጥበት?
በዛብህ፡- ውበቱ አባተ ለእኔ በብዙ ነገሩ ምርጡ እና የተሻለው አሰልጣኝ ነው፤ ከኳስ ስልጠናው ባሻገር በቲዎሪ ትምህርቱ እንደዚሁም ደግሞ ከኳሱ ውጪም ህይወትህን በምን መልኩ መምራት እንዳለብህም ከሚነግርህ ነገር በመነሳት የሚያስተምርህ ነገር አለና እሱ ለየት ይልብኛል፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስ ተጨዋችነት ላይ የቱ አይነት የኳስ ፍልስፍና ይመችሃል?
በዛብህ፡- ኳስን ፖሰስ አድርጎ መጫወትን፤ ውበቱ አባተ ብዙ ጊዜ በእዚህ ዙሪያም ይናገራል፤ ኳስን በያዝክ እና ፖሰስ አድርገህ በተጫወትክ ቁጥር ያን ማድረግህ ሁሉጊዜ ማጥቃትም መከላከልም ነው ይልሃልና ኳስን ተቆጣጥሮና ይዞ በመጫወት ላይ አምናለሁ፤ ምክንያቱም ኳስ በያዝክ ቁጥር ነው ማጥቃትም መከላከልም የምትችለው፡፡
ሊግ፡- ከባህር ማዶ የማን ደጋፊ ነህ?
በዛብህ፡- የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊ ነኝ፡፡
ሊግ፡- ብዙ የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊዎች ሊቨርፑል የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ እንዲያነሳ አይፈልጉም፤ አንተም እንደዛው ነህ?
በዛብህ፡- በፍፁም፤ ብዙ የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊዎች የእኔን ጓደኞች ጨምሮ ሊቨርፑል የሊጉን ዋንጫ እንዲያነሳ አይፈልጉም፤ እኔ ግን በእዛ ደረጃ አላምንም፡፡ የተሻለ ቡድን ዋንጫውን እንዲወስድም ነው ሁሌም የምፈልገው፤ ሊቨርፑልን ደግሞ አሁን እንደተመለከትኩት ባለው ብቃት ይሄ ድል ዘንድሮ ይገባዋል፤ በተለይ ደግሞ የቡድኑን አሰልጣኝ የርገን ክሎፕን ተጨዋቾቹን ሜዳ ላይ በሚመራበት መልኩም ሆነ ዘንድሮ ባለው የማሰልጠን ብቃት በጣም ስለምወደው ይሄን ዋንጫ ሊቨርፑል እንዲያነሳው እፈልጋለው፡፡
ሊግ፡- ከባህር ማዶ ተጨዋቾች ውስጥ የአንተን ቀልብ የትኛው ተጨዋች ይስበዋል?
በዛብህ፡- ለእኔ ክርስትያኖ ሮናልዶ የተለየ ተጨዋች ነውና እሱ ነው ሁሌም ቀልቤን የሚስበው፤ የእሱን ቪዲዮም ነው ብዙ ጊዜ የምመለከተው፤ እሱ አሁን ኳስ ያቆማል ብዬም በተደጋጋሚ ጊዜ ራሴንም እጠይቃለውና እሱን ካላየው ደስ እንደማይለኝም በዚህ አጋጣሚ መናገር እፈልጋለው፡፡
ሊግ፡- በባህሪህ በምን መልኩ የምትገለፅ ተጨዋች ነህ?
በዛብህ፡- ሁልጊዜም በሜዳ ውስጥና ከሜዳ ውጪ የተለያየው አይነት ተጨዋች ነኝ፤ ሜዳ ውስጥ ክፉ ባህሪ የለኝም፡፡ ሜዳ ከገባው በኋላ በምሠራው ስራ ላይ ማንም ሠው ፋውል ይሰራብኝም እኔም ልስራ ነገሮችን በይቅርታ የምተላለፍ አይነት ሰው ነኝ፤ በስራዬም ሲሪየስ ነኝ፡፡ ከሜዳ ውጪም ብዙ አስቸጋሪ ባህሪ የለኝም፡፡ ከጓደኞቼ ጋር በመዋል እጫወታለሁ፡፡ ሠዎች እረዳለው፤ ለሠዎች አዛኝ ነኝ፤ ሳቂታም ነኝ፤ ከዚህ ውጪ ሌላ የተለየ ባህሪህ የለኝም፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳሱ ላይ ባሳለፍከው ህይወት ደስተኛ ነህ? የተከፋህበት አጋጣሚስ አለ?
በዛብህ፡- አብዛኛው ህይወቴ የተደሠትኩባቸው ናቸው፤ የተከፋሁበት ጊዜ ቢኖር ደግሞ አምና የሊጉን ዋንጫ ያጣንበትን ብቻ ነው፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስን በልጅነት ዕድሜ ስትጫወት በቤተሰብ ዘንድ ፍቃድን ታገኝ ነበር? ለዛሬ ደረጃ የደረስከውስ በቀላሉ ነው?
በዛብህ፡- የእግር ኳስን ከልጅነት ዕድሜዬ አንስቶ ስጫወት በቤተሰብ ዘንድ ፈፅሞ ፈቃድን አላገኝም ነበር፤ ብዙ ነገሮችን አሳልፌም ነው ለዛሬ ደረጃም ላይ የደረስኩት፤ ያኔ ኳሱን ስጫወት በቤቱ ውስጥ ከሚገኙት ወንድ ልጆች መካከል እኔ የመጨረሻው ልጅ ነበርኩና ስራ እሰራና ትምህርትም እማር ስለነበር ከእኔ ብዙ ነገር ስለሚጠበቅ ብዙ ጫና ኖሮብኝም ነበር ኳሱን የምጫወተው፤ በግድ እና ጊዜዬን አጣብቤም ነው ኳስ እጫወትም የነበረው፤ ኳስ ተጫውቼ ስመጣም ቤት ውስጥ ዱላ ይጠብቀኝም ነበር፤ ያም ሆኖ ግን ከእለት እለት ዱላውም ቢኖር ኳሱን እየተጫወትኩ በመጓዝ የዛሬ እዚህ ደረጃ ላይ ልደርስ ችያለው፤ በኋላም ላይ ነው አባቴ የ12ኛ ክፍል ትምህርቴን ጨርሼ ዩኒቨርሲቲ መግባቴን ብቻ የሚያውቅ ቢሆንም፤ እኔ ግን በኳሱም ለሙገር የፕሮጀክት ቡድን በአቶ አዳነ አማካኝነት ተመልምዬና ተመርጬም ነው ወደ ኳሱ ውስጥም ዘልቄ መግባቴን በልምምድ ወቅት ጉዳት ደርሶብኝ እቤት በመጣሁበት ሰዓት ነው በማወቁ ከዛ በኋላ ፈቃድ ተሰጥቶኝ ወደ ኳስ ዓለሙ ዘልቄ ሙሉ ለሙሉ የገባሁት፡፡
ሊግ፡- ጋሽ አዳነን ስላነሳካቸው ነው፤ እሳቸው እንዴት ነው የሚገለፁት?
ሊግ፡- ጋሽ አዳነ ገ/የሱስ በምልመላ ሙያቸውም ሆነ በአሰልጣኝነታቸው የተለዩ ሰው ናቸው፤ በእይታ ብቃታቸው ሀገራችን አለኝ ከምትላቸው ባለሙያዎች መካከል ስማቸው ሁሌም የሚነሳ ነው፡፡ ታላላቅ ተጨዋቾችን ጨምሮ ብዙ የፕሪምየር ሊግ ተጨዋቾች በእሳቸው ምልመላም ነው የመጡት፡፡ በእግራቸው ሁሌም መንገድን በተደጋጋሚ ይሄዱና ይቆማሉ፤ ህፃናቶችንም ያዩና ይመለምላሉ፤ ልክ እኔን እንደመለመሉበት መንገድ ማለት ነው፤ በሙያቸው ጥሩ እውቀት እንዳላቸው ያስታውቃልና በብዙ ነገር ለእሳቸው የተለየ ቦታ ነው ያለኝ፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ?
በዛብህ፡- በእግር ኳስ ተጨዋችነት የእስካሁን ጉዞዬ ቤተሰቦቼ ለእኔ እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ ጥሩ አስተዋፅኦ አበርክተውልኛልና ሊመሰገኑ ይገባል፤ ከሁሉ በላይ ደግሞ የቀድሞው እግር ኳስ ተጨዋች የሆነው ታላቅ ወንድሜም ብዙ ነገርንም አድርጎልኛልና በምስጋናው በኩል ለእሱም የተለየ ቦታ አለኝ፤ ሌላ ሳልጠቅሳት የማላልፋት ፍቅረኛዬን ቅድስት አመነን ነው፤ የደብረታቦር ተወላጅ የሆነችው እና በወላይታ አድጋ የኖረችው ይህቺ የፍቅር አጋሬ የመቐለ ዩንቨርስቲ ተማሪ ሆና ሳለ እኔ ደግሞ ከዛማሊክ ጋር በነበረን ጨዋታ ላይ እዛ ሳገኛትና ትውውቅ ባደረግንበት ሰዓት በጊዜው ጥሩ ሙድ ላይ ያልነበርኩበትም ጊዜ ነበርና ከዛን ጊዜ ጀምሮ በነበረን ትውውቅ ለእኔ የአሁን የህይወት መስመር የተሳካ መሆን መልካሙን ሁሉ አድርጋልኛለችና እሷንም በጣሙን ማመስገን እፈልጋለው፡፡