Google search engine

“ለኢትዮጵያ ቡና የፈረምኩት ራሴን በትልቅ ደረጃ ላይ ማየት ስለፈለግኩኝ ነው” ሄኖክ ደልቢ /ኢትዮጵያ ቡና/

“ለኢትዮጵያ ቡና የፈረምኩት ራሴን በትልቅ ደረጃ ላይ ማየት ስለፈለግኩኝ ነው”

ሄኖክ ደልቢ /ኢትዮጵያ ቡና/

በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ሻምፒዮና ለኢትዮጵያ ቡና ለመጫወት በክረምቱ የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት ፊርማውን አኑሯል፤ ተወልዶ ያደገው በሐዋሳ ከተማ ውስጥ ነው፤ ሄኖክ ደልቢ ይባላል፤ በእዛም የውልደት እና የእድገት ቆይታው ለሐዋሳ ከተማ ክለብ ተጫውቶ ካሳለፈ በኋላ ነው ወደ ኢትዮጵያ ቡና ያመራው። ኢትዮጵያ ቡናን በመቀላቀሉ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማው የሚናገረው የአማካይ ስፍራ ተጨዋቹ ከሊግ ስፖርት ጋዜጠኛው  መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ ጋር በተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ ቆይታን አድርጓል።

ሄኖክ ለሊግ ስፖርት የሰጠው ቃለ-ምልልስም በሚከተለው መልኩም ቀርቧል፤ ተከታተሉት።

ሊግ፦ በቅድሚያ ለቃለ-ምልልሱ ፈቃደኛ ስለሆንክ ከልብ እናመሰግናለን?

ሄኖክ፦ እኔም የጋዜጣችሁ አምድ እንግዳ አድርጋችሁኝ ስለጋበዛችሁኝ ከልብ አመሰግናችኋለሁ።

ሊግ፦ በክረምቱ የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት ከሐዋሳ ከተማ ወደ ኢትዮጵያ ቡና ዝውውርን አድርገሃል፤ የተሰማህ ስሜት ምን ይመስላል?

ሄኖክ፦ ኢትዮጵያ ቡና ትልቅ ቡድን ነው፤ በብዙዎቹ ዘንድም የሚወደድ ነው። ወደዚህ ቡድን በመምጣቴ የተሰማኝ ስሜት የተለየ ነው። ምክንያቱም ብዙ ደጋፊ ባለው ክለብ ውስጥ መጫወት መቻል መታደል ስለሆነና ከእዛም ባሻገር  በኳሱም ራስህን አንድ ደረጃ ከፍ ወደምታደርግበት ቡድን ስትመጣና ብዙም ያላሳካካቸውን ድሎችንም ለማግኘት የምትመኘው ቡድንም ስለሆነ ወደ ቡና በመምጣቴ በጣም ደስተኛ ነኝ።

ሊግ፦ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ በሐዋሳ ከተማ ክለብ ውስጥ ነው  ቆይታን ያደረግከው፤  በእስካሁኑ የቡድንህ ጉዞ ስኬታማ ነበርኩ ማለት ትችላለህ?

ሄኖክ፦ በፍፁም፤  ያም ሆኖ ግን እንደ አንድ ቤቱ ውስጥ ከስር  እንዳደገ ተጨዋች ደግሞ  ጉዞዬ በዋንጫ ድሎች ባይታጀብም ጥሩ ቆይታ ነበረኝ። ቆይታዬ ጥሩ ቢሆንም  የሊጉን ዋንጫ ባለማንሳታችን ደግሞ በጣም ነው የሚቆጨኝ።

ሊግ፦ ለወጣት ቡድኑ ስትጫወት ደግሞ ቆይታህ በዋንጫ የታጀበ ነበር?

ሄኖክ፦ አዎን፤ ያኔ ጠንካራና ምርጥ ቡድን ነበረን። የእኛ ቡድን ደግሞ ወጣቶች ላይ ብዙ ጊዜም ነው ውጤታማም የሚሆነው።

ሊግ፦ ወደ ኢትዮጵያ ቡና የተዛወርክበት መንገድ ምን ይመስላል? ከሌሎች ክለቦችስ ጥያቄ አልቀረበልህም?

ሄኖክ፦ ቀርቦልኛል፤ ያም ሆኖ ግን ጥያቄን ካቀረቡልኝ ቡድኖች ውስጥ የእኔ ምርጫ  የሀገሪቱ ትልቅ ክለብ የሆነው ኢትዮጵያ ቡና ነው።  ኢትዮጵያ ቡና ሁሌም ልጫወትለት የምመኘው ቡድን ነው  ከእዛም ውጪ የሚመጡብኝን ፈተናዎችንም በእዚሁ ክለብ ውስጥ  መጋፈጥን ስለፈለግኩና ነገም ላይ  ራሴን በትልቅ ደረጃ ላይ ማየትንሞ ስለፈለግኩኝም  ነው በምንም ነገር ወደ ኋላ ሳልል  ጥያቄያቸውን ተቀብዬ ልፈርምላቸው የቻልኩት።

ሊግ፦ ወደ ኢትዮጵያ ቡና ከማምራትህ በፊት ስለ ክለቡ ምን አይነት እውቀቱና ግንዛቤው አለህ?

ሄኖክ፦ ብዙም ግንዛቤውና እውቀቱ ባይኖረኝም ክለቡ ከእኔ አጨዋወት ጋር ይሄዳል የሚለውን ነገር ግን በሚገባ ተመልክቼበታለሁ።

ሊግ፦ ኢትዮጵያ ቡናን በተቃራኒነት የተፋለምክባቸው ብዙ አጋጣሚዎች አሉ?

ሄኖክ፦ አዎን፤ ከእነሱም ጋር ሆነ ከቅ/ጊዮርጊሶች ጋር ተቃራኒ ሆነህ ስትጫወት በኢትዮጵያ ውስጥ የምንገኝ አጠቃላይ ተጨዋቾች  ሁለቱ ቡድኖች ብዙ ደጋፊዎች ያላቸው ስለሆኑና ትልቅም ቡድን ስለሆኑ ራሳችንን በደምብ ለማሳየትና ያለንንም አቅም አውጥተን ለመጫወት ወደ ሜዳም ስለምንገባም እኔም ቡናን በተቃራኒነት በገጠምንበት ጨዋታዎች ላይ ደስ ብሎኝና ጥሩም ሆኜ የተጫወትኩባቸው ጊዜያቶች ነበሩ።

ሊግ፦ አሁን ላይ  እግር  ኳስ ተጨዋች ነህ? ባትሆን ኖሮስ?

ሄኖክ፦ የአባቴን እና የወንድሜን ሁለቱም ከመኪና ጋር በተያያዘ ስለሚሾፍሩ የእነሱን ፈለግ እከተል ነበር፤ ያ ካልሆነ ደግሞ በትምህርቴም  በኳሱ ምክንያት አቆምኩት እንጂ የሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ትምህርቴን እየተማርኩ ነበርና በእዛ ተመርቄ ስራዬን እሰራ ነበር።

ሊግ፦ ወደፊት ይህን ትምህርትህን ታጠናቅቃለህ?

ሄኖክ፦ በሚገባ ነዋ!

ሊግ፦ የእግር ኳስን መጫወት ስትጀምር ለአንተ ተምሳሌትህ ማን ነበር?

ሄኖክ፦ በሐዋሳ ከተማ ውስጥ ያኔ ብዙ የብሔራዊ ቡድን የማውቃቸው ተጨዋቾች ነበሩ፤ እነ ሙልጌታ ምህረትን እያየው ነው ያደግኩት አብሬው የመጫወት ዕድሉም ገጥሞኛል። ያ በመሆኑ እሱን እንደ ተምሳሌትም ነው የማየው። ከእሱ ሌላ ደግሞ ከሙሉዓለሞ ረጋሳ ጋርም አብሬው የመጫወት ዕድሉ ገጥሞኛል። እሱ ጥሩ ችሎታ ነው  ያለው። በፊት ሲጫወት ባላየውም በአንድ አጋጣሚ ሲጫወት አይቼው ስላደነቅኩት እሱንም እንደ ተምሳሌቴ ላየው ችያለሁ።

ሊግ፦ ከባህርማዶ ተጨዋቾች ውስጥስ?

ሄኖክ፦ የፖል ስኮልስ አድናቂ ነኝ።

ሊግ፦ ከእግር ኳስ ውጪ ያለህን ጊዜ በምን ታሳልፋለህ?

ሄኖክ፦ ብዙውን ጊዜዬን የማሳልፈው ልምምድን በመስራት ነው፤ ከእዛ ውጪ ያለውን ደግሞ በካምፕ ውስጥ ከቡድን ጓደኞቼ ጋር ሆኜ በመጫወትና ፊልሞችንም በማየት ነው።

ሊግ፦ ወደ ሐዋሳ ከተማ ለመምጣት ለሚያስብ ሰው አንድ ነገርን አስጎብኝ ብትባል ምን ነገርን ታስጎበኛለህ?

ሄኖክ፦ ሐዋሳ የፍቅር ከተማ ናት። እዛ ለሚመጣ ሰው የማስጎበኘውም የፍቅር ሀይቅን ነው። ከዛም ዓሳን አበላዋለሁ።

ሊግ፦ የተለየ የምግብ አመጋገብ አለህ?

ሄኖክ፦ የለኝም።

ሊግ፦ ከምግብ አጥብቀህ የምትወደው?

ሄኖክ፦ በጣም የምወደው ፓስታን ነው።

ሊግ፦ የደቡብ ልጆች ግን በአብዛኛው ለጥሬ ስጋ ነው ፍቅር ያላቸው?

ሄኖክ፦ ስጋን እኮ እኔም አልጠላም። እንደ ማንኛውም ሰውም እመገበዋለሁ።  ሲበዛ ግን ጥሩም አይደለምና ለእዛም ነው የቅድሚያ ምርጫዬን ፓስታ ያደረግኩት።

ሊግ፦ ወደ ኢትዮጵያ ቡና ስታመራ ያጋጠሙህ የተለዩ ነገሮች አሉ?

ሄኖክ፦ ወደ ቡድኑ ሳመራ ለእኔ እድገትን፣ ከፍታንና መልካም ነገሮችን የሚመኙ ሰዎች አሉና ቤተሰቤን ጨምሮ በመጀመሪያ እንኳን ደስ ያለህ ነው ያሉኝ። ሲቀጥል ደግሞ በርትቼ መስራት እንዳለብኝም ነው የነገሩኝ።

ሊግ፦ ኢትየጵያ ቡናን ከተቀላቀልክ በኋላ አንተን ጨምሮ ብዙዎቻችሁ ተጨዋቾች ከደጋፊው ጋር በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ከተጨዋቾች ጋር ትውውቅን አድርጋችሁ ነበር፤ በእዛ ዙሪያ የምትለው ነገር ካለ?

ሄኖክ፦ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ እንዲህ ያለ ትውውቅ ሲደረግ ለመጀመሪያ ጊዜ ይመስለኛል። ይሄ የትውውቅ ፕሮግራምም በእኛ ሀገር ያልተለመደ ስለሆነም ቡናን ሁሌም እንዲታወስም ያደርገዋል። ይሄ አይነት ትውውቅ ብዙ ጊዜ የተለመደው በውጪው ዓለምም ነው። ወደ እኛ ሀገር መምጣቱ የተጨዋቾችን የመጫወት ፍላጎት ከመጨመር ባሻገር  ከፍተኛ ሀላፊነት እንዲሰማክም ስለሚያደርግ ለወደፊቱም ቢቀጥል ጥሩ ነው፤ ከእዛ ውጪም በእዚህ መልኩ ለቡና ፈርሜ ከደጋፊው ጋር ትወውቅ ካደረጉት ተጨዋቾች መካከል አንዱ በመሆኔም ዕድለኛ ነኝ።

ሊግ፦ በአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ለኢትዮጵያ ቡና እየተጫወትክ ይገኛል፤ በቡና ደጋፊዎች  ፊት መጫወት ያለው  ስሜት ምን ይመስላል? የትናንቱን ሳይጨምር ስላለፉት ጨዋታዎቻችሁስ ምን ትላለህ?

ሄኖክ፦ በእግር ኳስ ህይወቴ እንደ ኢትዮጵያ  ቡና ያለ ደጋፊ አጋጥሞኝ አያውቅምና በእነሱ ፊት ለመጫወት መቻሌ ደስ የሚል ስሜት እንዲሰማኝ አድርጓል። በእነዚህ ደጋፊዎች ፊት ስትጫወት ሁሌም ትነቃቃለህ። አስገራሚ ድጋፍንም ነው የሚያደርጉት። ወደ ጨዋታዎቹ ሳመራ ከመጀመሪያው ሁለተኛው ተሽለን ተገኝተናል። በእስካሁኑ እንቅስቃሴያችንም ደስተኛ ያልሆነ ደጋፊ አለን ብዬም አላስብም። በቀጣይነት ደግሞ ብሄራዊ ቡድን ያሉት ሲመጡና ሲቀላቀሉን ደግሞ የበለጠ ጠንካራም እንሆናለን፤ ምርጥ የሆነ ቡድንንም እንገነባለን።

ሊግ፦ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎ ኢትዮጵያ ቡናን እንዴት እንጠብቀው?

ሄኖክ፦ ኢትዮጵያ ቡና ሁሌም ቢሆን ለሻምፒዮናነት እንደሚጫወት ቢታወቅም ቡድኑ ያን ጥሩ የሚባል ውጤት እንዲያመጣ ከተፈለገ ጊዜና ትዕግስት ያስፈልጋል። ያን ካገኘን የተሻለ ነገር የሚሰራ ቡድን አለን። በዘንድሮ የውድድር ዘመን ተሳትፎአችንም ጥሩ ውጤት ለማምጣት እያንዳንዱን ጨዋታዎች እንደ ዋንጫ በመቁጠር ነው የምንጫወተው። ማሸነፍ ስንችልም የሊጉን ዋንጫ የማናነሳበት ምንም ምክንያት የለም።

ሊግ፦ በእግር ኳስ ጨዋታ ዘመንህ  የራስህ ራዕይህ እና ግብህ ምንድን ነው?

ሄኖክ፦ ማንም እግር ኳስ ተጨዋች ኳስን ሲጀምር ከሚጫወትበት ክለብ ጋር ዋንጫን ማንሳት ቀጥሎ ደግሞ ለሀገሩ ብሄራዊ ቡድን በመመረጥ መጫወት መቻልና በመጨረሻ ደግሞ ፕሮፌሽናል ተጨዋች ሆኖ በባህርማዶ ክለቦች ውስጥ መጫወት ነውና የእኔ እልምና ፍላጎቴ ይሄ ነው።

ሊግ፦ አቡበከር ናስር በደቡብ አፍሪካው ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ክለብ ውስጥ በጥሩ ብቃቱ እየተጫወተ ይገኛል? እሱን ስትመለከት እኔስ የሚል ስሜት በውስጥህ አልተፈጠረብህም?

ሄኖክ፦ በደምብ እንጂ፤ ምክንያቱም የእሱ ወጥቶ መጫወት ነገም ላይ እኔስ ለምን ፈለጉን አልከተልም፤ እንደ እሱ ወጥቶ ለመጫወትስ ምን መስራት አለብኝ እንድትል ስለሚያደርግህ ያን ዕድል ለማግኘት በርትቼ እሰራለሁ። በአቡኪ ወጥቶ መጫወትም በጣም ደስተኛ ነኝ። የለፋ ተጨዋች ስለሆነም እሱ የሚገባውን ትልቅ ዕድልም ነው ያገኘው። ትልቅ ደረጃ ላይ እንዲደርስም እመኝለታለሁ።

ሊግ፦ በመጨረሻ ?

ሄኖክ፦ በእግር ኳስ ህይወቴ ዛሬ ላይ ለደረስኩበት ደረጃ በቅድሚያ ፈጣሪዬን ማመስገን እፈልጋለሁ። ሲቀጥል ቤተሰቦቼ አሉ፤ በተለይም ደግሞ እናቴን። ከእዛም አሁን ላይ ለእኔ አጨዋወት ትክክለኛ ሰው ነህ ብሎ ወደ ኢትዮጵያ ቡና እንድመጣ ያደረገኝን አሰልጣኝ ተመስገን ዳናን እና ከእዚህ ቀደም ያሰለጠኑኝን ውበቱ አባተን፣ ሙልጌታ ምህረትን፣ አዲሴ ካሳንና አሰልጣኝ ካልሆኑት ደግሞ ግሩም ባሻዬን ላመሰግናቸው እፈልጋለሁ።

 

 

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this: