Google search engine

“በመቐለው ሽንፈት ቁጭት ስላለብን ውጤቱን እንቀለብሰዋለን” ሽመክት ጉግሳ /ፋሲል ከነማ/ “ወደ ጎንደር ያመራነው የድል ውጤትን ልናስመዘግብ፤ መሪነታችንንም ልናጠናክር ነው”   ያሬድ ሀሰን /መቐለ 70 እንደርታ

በመሸሻ ወልዴ /G.BOYS/

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ18ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬና ነገ ይከናወናሉ፤ በመቐለ 70 እንደርታ የሊጉ መሪነት እየተካሄደ ያለው ይኸው የሊግ ውድድር በርካታ ግጥሚያዎችን ሲያስተናግድም የሚጠበቁ ጨዋታዎች ያሉ ሲሆን ከእነዚህም መካከል በጎንደሩ ፋሲለደስ ስታዲየም በቀድሞው የምግብ ድርጅት እና የአዳማ ከተማ ተጨዋች አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በሚሰለጥነው ፋሲል ከነማ  እና በቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የእርሻ ሰብል ተጨዋች አሰልጣኝ ገብረ መድህን ኃይሌ  በሚሰለጥነው መቐለ 70 እንደርታ ክለቦች መካከል የሚካሄደው ጨዋታ ከፍተኛ ትኩረትን ስቧል፡፡

የፋሲል ከነማ እና የመቐለ 70 እንደርታ የነገው ጨዋታ የሚካሄደው የሊጉ መሪ መቐለ 70 እንደርታ በ17 ጨዋታዎች 39 ነጥብን በያዘበት እና በ4ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ፋሲል ከነማ ደግሞ 29 ነጥብን በያዙበት ሁኔታ ላይ በመሆኑ የሁለቱ ጨዋታ መሪው ክለብ ካሸነፈ በነጥብ የሚርቅበት ባለሜዳው ቡድን ካሸነፈም የነጥብ ልዩነቱን የሚያጠብበት ሁኔታ ስላለ ጨዋታው ጥሩ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የፋሲል ከነማ እና የመቐለ 70 እንደርታን ጨዋታ አስመልክቶ እንደዚሁም ደግሞ በሊጉና በክለቦቻቸው ወቅታዊ  አቋም  ዙሪያ ከሁለቱ ቡድኖች ተጨዋቾች መካከል ጥሩ እንቅስቃሴ ከሚያሳዩት ውስጥ የፋሲል ከነማውን ሽመክት ጉግሳ እና የመቐለ 70 እንደርታውን ያሬድ ሀሰንን ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ ጠይቋቸው ተጨዋቾቹ የሚከተለውን ምላሽ ለሊግ ስፖርት ጋዜጣ ሰጥተዋል፡፡

ሊግ፡- የፋሲል ከነማ እና የመቐለ 70 እንደርታ የእሁድ ጨዋታ በከፍተኛ ጉጉት ተጠብቋል፤ ለግጥሚያው ያደረጋችሁት ዝግጅት ምን ይመስላል? ማንስ የጨዋታው አሸናፊ ይሆናል?

ሽመክት፡- የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ የአሁን ሰአት ላይ ካለው ወቅታዊ አቋም በመነሳት የነገውን የእሁድ ጨዋታ ለማድረግ የተዘጋጀው ተጋጣሚውን አሳማኝ በሆነ የኳስ እንቅስቃሴ በልጦና ግጥሚያውን አሸንፎም ከሜዳ ለመውጣት ነው፡፡

ከመቐለ 70 እንደርታ ላለብን የነገው ጨዋታም ፍልሚያውን የግድ ማሸነፍ እንዳለብን ስለማምን እና በጨዋታው ዙሪያ  ሁላችንም ስለተነጋገርንበትም ጨዋታውን በእርግጠኝነት እኛ እናሸንፋለን፡፡

ያሬድ፡- መቐለ 70 እንደርታ ፋሲል ከነማን ለሚፋለምበት የነገው የሜዳው ውጪ ጨዋታ በተለየ መልኩ ያደረገው ዝግጅት የለም፤ ወደ ጎንደር ተጉዘን ግጥሚያውን የምናደርገው አቻ ለመውጣት ሳይሆን ጨዋታውን ለማሸነፍ ነው፤ የሁለተኛው ዙር እያንዳንዶቹን ግጥሚያዎችም የትም ቢሆን ብንጫወት ለማሸነፍም ነው ወደ ሜዳ የምንገባው እና ከፋሲል ጋር በሚኖረን ጨዋታ የሚመጣውን ውጤት ከ90 ደቂቃ በኋላ እንመለከተዋለን፡፡

ሊግ፡- የፋሲል ከነማ ተጨዋቾች መቐለ 70 እንደርታን፤ የመቐለ 70 እንደርታም ተጨዋቾች ፋሲል ከነማን  እናሸንፋለን በማለት ከወዲሁ አስተያየቶችን እየሰጡ ነው፤  ይህንን የአሸናፊነት ድል የሚጎናፀፈው  ትክክለኛው ቡድን ማን  ይሆናል?

ሽመክት፡- አሸናፊ የምንሆነውማ እኛ ነን! የፋሲል ከነማ ክለብ የመጀመሪያው ዙር ላይ ወደ መቐለ ተጉዞ ጨዋታውን ባደረገበት ጊዜ  አወዛጋቢ በሆነ ሁኔታ 1ለ0 በሆነ ጠባብ ውጤት ቢሸነፍም ቡድኑ የተሸነፈው ጥሩ አቋም ኖሮት ነው፤ በእዚያ ጨዋታም ሁላችንም በመሸነፋችን ቁጭት ያለብን እና የተጋጣሚያችንን አቋምም በሚገባ የተመለከትንም ስለሆነ ለምንም ነገር ወደኋላ ሳንል የመቐለው  ጨዋታ ላይ በደረሰብን ሽንፈት ቁጭት ስላለብን አሁን ደግሞ እኛ በተራችን ጨዋታውን አሸንፈን  ውጤቱን እንቀለብሰዋለን፡፡

ያሬድ፡- ፋሲሎች ከእኛ መቐለ 70 እንደርታዎች ጋር  የነገውን ጨዋታ ከማድረጋቸው በፊት ጨዋታውን እናሸንፋለን ሊሉ ይችላሉ፤ እኛም እኮ ወደዛ ስናመራ ግጥሚያውን  ልንሸነፍ አንሄድም፤ እኛ መቐለዎች  የነገውን ጨዋታ የምናደርገው ከማንኛውም ቡድን ጋር ማለትም ከ15ቱም ቡድኖች ጋር እንደምንጫወተው ጨዋታ ተጫውተን እና ያለንንም አቅም አውጥተን ነው ከሜዳው ላይ ጣፋጭ የሆነውን 3 ነጥብ ይዘን ለመውጣት የተዘጋጀነውና የጨዋታው አሸናፊ የምንሆነው እኛ ነን፡፡

ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ያላችሁ ወቅታዊ አቋም ምን ይመስላል?

ሽመክት፡- ፋሲል ከነማ በሜዳው ላይ የጨዋታ እንቅስቃሴውም ሆነ በሞራል ደረጃ የአሁን ሰአት ላይ የሚገኝበት ሁኔታ ጥሩ እና ክለቡንም በጣም የሚያበረታታው ነው፤ ይሄንን ጥሩ አቋማችንን አጠናክረን ልናስቀጥለውም ተዘጋጅተናል፡፡ ከዛ ውጪም ከዚህ በኋላ የሚኖሩንን ጨዋታዎች በደረጃው ሰንጠረዥ ወደመሪዎቹ የሚያስጠጋንን ውጤቶችም የምናስመዘግብበት ስለሆነ ስራችንን በከፍተኛ ፍላጎት እና ጥረቶችም ለማከናወን  የምንገኝበት ሁኔታ ላይ ስላለን ይሄ ህልማችን የሚሳካ ነው የሚሆነው፡፡

ያሬድ፡-  መቐለ 70 እንደርታ በሊጉ ላይ ያለው ወቅታዊ አቋሙ በአህምሮ ዝግጁነትም ሆነ በሜዳ ላይ ውጤታማነቱ ጥሩ ነው፤ ለእዚህም ነው መሪነታችንን አሁን ድረስም አስጠብቀን ለመቆየት የቻልነው፤  በሊጉ የሁለተኛው ዙር ላይም ጥሩ የውድድር ጅማሬን ከወዲሁ እያሳየን ነው፤ በጉዳት ላይ የነበሩት አንዳንድ ተጨዋቾቻችንም ከጉዳታቸው አገግመው ወደሜዳ የተመለሡና  አማኑኤል ገ/ሚካኤልንም የመሰለ ውጤታማ የአጥቂ ስፍራ ተጨዋቻችንም ከኦሎምፒክ ብሄራዊ ቡድን የጨዋታ ግዴታው መለስ ስኳዳችንን በመቀላቀሉ እንደዚሁም  በሁለተኛው ዙር የዝውውር መስኮትም ሄኖክ ኤሳያስን ወደ ቡድናችን ያስመጣንበት ሁኔታም ስላለ ቡድናችን በሁሉም መልኩ ጠንካራ ሆኖ ይቀርባልና አሁን ላይ ያለን  አቋም  ጥሩ እንደሆነ እያስመዘገብን የምንገኘው ውጤት ያመላከተልን ሆኖ ተገኝቷል፡፡

ሊግ፡- መቐለ 70 እንደርታ የነገ ተጋጣሚያችሁ ናቸው፤ እነሱን እንዴት ነው የምትገልፃቸው?

ሽመክት፡- መቐለ 70 እንደርታ በሊጉ የውድድር ተሳትፎአቸው ጠንካራ ክለብ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ያም ሆኖ ግን  ጥንካሬያቸው ከእኛ ቡድን ፈፅሞ አይበልጥም፤ የእኛ ጥንካሬ ከእነሱ ይበልጣል፤ ያንን ደግሞ በመጀመሪያው ዙር የእርስ በርስ ጨዋታችን ምንም እንኳን ሽንፈትን ብንጎናፀፍም በሜዳ ላይ የጨዋታ እንቅስቃሴም የተሻልን መሆናችንን አሳይተናልና በነገው ጨዋታም ይሄንን የሜዳ ላይ ጠንካራነታችንን በድጋሚ   የምናሳይ  ይሆናል፡፡

ሊግ፡-  አንተስ የነገ ተጋጣሚያችሁን ፋሲል ከነማዎችን እንዴት ነው የምትመለከታቸው?

ያሬድ፡- ፋሲል ከነማ ጥሩ ቡድን ነው፤ የተሻለም የተጨዋቾች ስብስብ አለው፤ ይሄንን ጥሩ ስብስባቸውንም  ከእኛ ሀገር በሜዳችን ላይ ሲጫወቱም ተመልክተናል፤ ያ ጥሩ መሆናቸው ግን እኛን ፈፅሞ አያሳስበንም እና በሁለታችን መካከል የሚደረገው የነገው ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር ይደረግበታልና በጨዋታው ላይ ከፍተኛ ፈተና እንደሚገጥመን እርግጠኛ ነኝ፡፡

መቐለ 70 እንደርታ ከፋሲልም፣ ከቅዱስ ጊዮርጊስም ከደደቢትም ሲጫወት ለተጋጣሚዎቹ የሚሰጠው የተለየ ግምት ባይኖርም የቡድኑን የተጨዋቾች ስብስብ ግን ሳላደንቅ አላልፍም፡፡  

ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ለማንሳት ያላችሁ እድል የቱን ያህል ነው?

ሽመክት፡- ፋሲል ከነማ የሊጉን ዋንጫ የማንሳት እድል  አሁንም አለው፤ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ሊጠናቀቅም እያንዳንዱ ቡድን ገና አስራ ሶስት ጨዋታዎች ይቀሩታል፤  ፋሲል ከነማም በመሪው ክለብ መቐለ 70 እንደርታ በ10 ነጥብ ተበልጦ ቀሪዎቹን ጨዋታዎች እየጠበቀ ይገኛል እና የሊጉን ዋንጫ የማንሳት እድላችን ገና ስላላበቃ ይሄን እድል እስከመጨረሻው ጨዋታዎቹ ድረስ ይጠብቃል፡፡ ፋሲል ከነማ የሊጉን ዋንጫ ለማንሳትም ከፊቱ ያሉትንም ግጥሚያዎች እያሸነፈ መሄድ ይኖርበታል፤ በሜዳው ነገ በሚያደርገው ጨዋታም መቐለ 70 እንደርታን ስለሚያሸንፍ ከመሪው ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ 7 ያጠባል፡፡ ይሄ ደግሞ ወደዋንጫው ፉክክር እንድንገባ መንገዱን ይከፍትልናልና ዋንጫውን ልናነሳ የምንችልበት እድሉ አሁንም እንዳለን በእርግጠኝነት ለመናገር ይቻላል፡፡

ያሬድ፡- መቐለ 70 እንደርታ የሊጉን ዋንጫ የማንሳት እድሉ ከሁሉም ቡድኖች የተሻለ ብቻ ሳይሆን በእርግጠኝነትም ዋንጫውን የሚያነሳው ብቸኛው ክለብ እርሱ ነው፤ ይሄንን ያለምክንያትም አይደለም የምነግርህ፤ የሊጉ የሁለተኛው ዙር ጅማሬያችን ጥሩ ነው፤ የእኛ ቡድን በሁለት ጨዋታዎች አራት ነጥብንም ሊያስመዘግብ ችሏል፡፡ ብዙ ጎልም አስቆጥሯል፡፡ ይሄን ያሳካ ከእኛ እና ከአንድ ሌላ ቡድን ውጪ ስለሌለም መቀሌ 70 እንደርታ የዘንድሮ ሻምፒዮና ነው የሚሆነው፡፡

ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ያለፉትን ሳምንት ግጥሚያዎች የእናንተ ክለቦች የሆኑት ፋሲል ከነማም መቐለ 70 እንደርታም በአቻ ውጤት ነበር ያጠናቀቁት፤ ጨዋታዎቻችሁ ምን መልክ ነበራቸው?

ሽመክት፡- ወደሃዋሳ በመጓዝ ከሃዋሳ ከተማ ጋር ያደረግነውን ያለፈው ሳምንት ጨዋታችን ምንም እንኳን በጥቃቅን ስህተት ነጥብ ተጋርተን የወጣንበት ቢሆንም ከሜዳችን ውጪ እንደመጫወታችን በውጤቱ አልተከፋንም፤ ያ ግጥሚያ ብዙ ነገርን አስተምሮናል፡፡ በቀጣይ ጨዋታዎቻችን ላይ ስህተትን እንዳንሰራ እና በመጪዎቹ ጨዋታዎች ላይም ስህተቶቻችንንም እንድንቀንስ የሚያደርገን ግጥሚያ ሆኖ ስለተጠናቀቀ ለእኛ ግጥሚያው ጠቃሚም ሆኖልናል፡፡

ያሬድ፡- የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጋር የነበረን ያለፈው ሳምንት ጨዋታ ያንን ያህል በጎላ መልኩ ጥሩ ፉክክር ተደርጎበታል ብዬ ባላስብም እኛ ለጎል የሚሆን ኳስ አግኝተን ስለሳትን እንጂ ጨዋታውን ማሸነፍ እንችል ነበር፡፡ ግጥሚያውን ብናሸነፍ ኖሮም በጣም ደስ ይለንም ነበር፤ ያም ሆኖ ግን  እነሱ በጊዜ አስቀድመው ጎል አግብተውብን ስለነበር ጨዋታው በአቻ ውጤት ሊጠናቀቅ ችሏል፡፡ ይሄ ውጤትም ተከታያችን ካስመዘገበው ተመሳሳይ ውጤት አንፃር ብዙም የሚያስከፋን ስላልሆነ በቀጣዩ ጨዋታ ላይ ወደ አሸናፊነት መንፈሳችን እንመለሳለን፡፡

ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛ ዙር የጨዋታ ጅማሬውን እንዴት እየተመለከታችሁት ነው?

ሽመክት፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛው ዙር ፉክክር ጥሩ ጅማሬ እየተደረገበት ነው፤ ዋንጫውን ለማንሳት መሪው መቐለ 70 እንደርታ ተከታዮቹ ሲዳማ ቡና፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና እኛም እድሉ አለንና ይሄ ፉክክር እስከመጨረሻው ሰአት ድረስ  በጥሩ የፉክክር ሁኔታ ይቀጥላል፡፡

ያሬድ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛው ዙር ጅማሬን ከተፎካካሪዎቻችን ክለቦች አኳያ እንደተመለከትኩት  በውድድሩ  ከእኛ ክለብ የበለጠና  የተሻለ የሚባልም ውጤት ያመጣ ቡድን ማንም የለምና አሁንም ከወዲሁ እኛ የበላይነቱን ይዘናል፡፡ መቐለ 70 እንደርታ የሊጉን የሁለተኛው ዙር ሲጀምር ከሁለት ጨዋታዎች 4 ነጥብን አግኝቷል፤ በርካታ ግብም አስቆጥሯል፤ ከአንድ ክለብ በስተቀር ብዙዎቹ ከእኛ ያነሰ ነጥብን ነው ያስመዘገቡት እና የውድድሩን ጉዞ በቀጣይነትም ስገምተው እኛን የሚያስፈራን ምንም ነገር አይኖርምና የእዚህ ዓመት አሸናፊ እንሆናለን፡፡

ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛው ዙር ግጥሚያችሁን እስከመጨረሻው ሰአት ድረስ በምን መልኩ ልታስኬዱት ነው ያቀዳችሁት?

ሽመክት፡- ፋሲል ከነማ የአሁን ሰአት ላይ በጥሩ ሞራል ላይ ይገኛል፡፡ የሊጉን ዋንጫ ለማንሳትም እያንዳንዶቹን ግጥሚያዎችም ማለትም ነገ በሜዳችን ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር ከምናደርግው ጨዋታ ጀምሮ ማሸነፍ ስላለብንም ለእዛ በጥሩ መልኩ ተዘጋጅተናል፡፡

ያሬድ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛው ዙር ጅማሬያችን ጥሩ እና አበረታች ቢሆንም ይሄንን እስከ ውድድሩ ማብቂያ ድረስ ወደኋላ ሳናፈገፍግ ልናስቀጥለው ተዘጋጅተናል፡፡ መቐለ 70 እንደርታ በእዚህ የሊጉ ጉዞውም ምን ማድረግ እንዳለበት የሚያውቅ ክለብም ነው፤ ቡድናችን በቀጣይ የሊግ ጨዋታው ነገና ከነገ ወዲያም በአንዳንድ ጨዋታዎች ላይ ውጤት ቢበላሽበት እንኳን ያን በፍጥነት ማስተካከል የሚያስችል አቅም እና ያንን ውጤትም በሚሰጠው ስልጠና ሊለውጥ የሚችል ምርጥ አሰልጣኝም ስላለው ይሄን ደግሞ ከዚህ በፊትም ገጥሞን ውጤታችንን ያስተካከልንበት ጊዜም ስለነበር ክለባችን ከዚህ በኋላ እስከ ውድድር ዓመቱ መጨረሻ ድረስ በውጤታማነት ጉዞው ነው የሚቀጥለው፡፡

ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ በሚሰጧችሁ ድጋፎች የክለባችሁን ደጋፊዎች እንዴት ነው የምትገልፃቸው?

ሽመክት፡- የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች በሜዳችንም ሆነ ከሜዳችን ውጪ ስንጫወት ሁሌም ቢሆን ከአጠገባችን ሳይለዩ ባማረ ህብረ ዜማና ጭፈራ የሚደግፉን እና የሚያበረታቱን ናቸው፤ እነዚህን ደጋፊዎች ስታይም ከልብህ ኳስን እንድታጫወትም ያደርጉሃልና እኔ ብዙ ጊዜ ወደሜዳ ስገባ በእዛ መልኩ ነው ግጥሚያዎቼን የማደርገው፤ ስለዚህም እኛ ሁልጊዜም ቢሆን  እነሱን ለማስደሰት ነው የምንፈልገውና ከነገው ወሳኝ ጨዋታ ጀምሮም ይሄንን ልናሳያቸው ተዘጋጅተናል፡፡ በእዚሁ አጋጣሚም ደጋፊዎቻችን ለሚሰጡንም ድጋፍ ላመሰግናቸው እፈልጋለሁ፡፡

ያሬድ፡- የመቐለ 70 እንደርታ ክለብ ደጋፊዎች ቡድናቸውን ሲያበረታቱ ለተመለከተ እንደ 12ኛ ተጨዋች የሚቆጠሩ ናቸው፤ በእዚህ አመት ላስመዘገብነውም ስኬታማ ውጤቶች የእነሱን ከጎናችን መሆንና እኛን ማበረታታትም በጣም ጠቅሞናልና በዚህ በጣሙን ሊመሰገኑ ይገባል፡፡

ሊግ፡- በመጨረሻ……

ሽመክት፡- የፋሲል ከነማ  ተጨዋቾችም ሆኑ የእኛ ቡድን ደጋፊዎች  ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር የሚኖረንን የነገው  ጨዋታ ማሸነፍ እና አሸንፈንም የነጥብ ልዩነታችንን በማጥበብ ወደ ዋንጫው ፉክክር መግባትን አጥብቀን ስለምንፈልግ ይህንን ግጥሚያ የስፖርታዊ ጨዋነት በተላበሰበት መልኩ ለማከናወን በሁሉም መልኩ ዝግጁ ሆነናል፡፡

የፋሲል እና የመቐለ የመጀመሪያው ዙር ጨዋታ በጨዋነት የተጠናቀቀ በመሆኑ ነገም ይሄ ይደገማል፤ በሁለታችን መካከል በሚኖረው ፍልሚያም ቡድናችን ግጥሚያውን በሜዳው ላይ የሚያደርግ እና በሜዳው ከመጫወቱ አኳያም ጨዋታውን የማሸነፍ እድሉ ወደ እኛ ስለሚያጋድል ግጥሚያውን በመርታት ደጋፊዎቻችንን እናስደስታለን፡፡

ያሬድ፡- የትግራይ እና የአማራ ክልል ክለቦች የሆኑት መቐለ 70 እንደርታ እና ፋሲል ከነማ የመጀመሪያው ዙር ላይ ሲጫወቱ ግጥሚያው በሰላም የተጠናቀቀ እና የከዚህ ቀደሙንም የስፖርታዊ ጨዋነት ጥሰትም ከእንግዲህ እንደማይኖር ያሳወቀ እና  የረብሻ ሁኔታዎችም እንዲረሹ ያደረገ ግጥሚያ ስለሆነ ነገ የሚኖረውም የሁለታችን ፍልሚያ ኳስን የሰላማዊ ጦርነት ብቻ በማድረግ የምናከናውነውና እኛም ጨዋታውን አሸንፈን ደጋፊዎቻችንን የምናስደስትበትም ይሆናል፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this: