Google search engine

“ዘንድሮ በተለይ በተሳሳተ የዳኛ ውሳኔ እየተጎዳን ነው” “ከእኛና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውጪ ሌላ የዋንጫ ተፎካካሪ አለ ብዬ አላምንም” በረከት ደስታ /መቻል/

“ኢትዮጵያ ሰላም ሆና ሁሉም ሰው በየስራ ዘርፉ እየለፋ  ሰላም ገብቶ እንዲወጣ  እመኛለሁ እንደ እግርኳስ ደግሞ በህይወት  እያለሁ ሀገሬ ለአለም ዋንጫ አልፋ  ማየት እመኛለሁ” ይላል እንግዳችን በረከቴ ደስታ… የመቻል የአመቱጠጉዞ ምርጥ መሆኑን ተናግሮ በአምስት ነጥብ ብንበለጥም እስከ መጨረሻው እንታገላለን   በክለባችን ውስጥ ያለው ለውጥም ምርጥ የሚባል ነው ሲል ይናገራል ….ከሊጉ ዮሴፍ ከጸለኝ ጋር ባደረገው ቆይታ ለቀረቡለት ጥያቄዎች ምላሹን ሰጥቷል።

ሊግ:-  በረከት ደስታና መቻል በሚገባ ተጣምረዋል ማለት ይቻላል…?

በረከት:- አዎ በደንብ እንጂ …በደንብም ተጣምረዋል በመቻል ደስተኛ ነኝ…. ጥሩ ጊዜ  እያሳለፍኩ ነው  አሪፍ ስብስብ  አለን ጥሩ የሚባልም ቦርድ አለን በቃ መቻል አሪፍ ሆኗል።

ሊግ:-  ከመሪው ንግድ ባንክ የያለው የነጥብ ልዩነት ወደ 5 ሰፍቷል…ተስፋ ቆረጣችሁ…?

በረከት:– በፍጹም ገና አራት ጨዋታ አለ…ሙሉ 12 ነጥብ ማለት ነው ልዩነቱ ደግሞ አምስት  ነው እስከ መጨረሻ መታገል እንጂ የምን ተስፋ መቁረጥ አመጣህ..? መቻል ቤት ተስፋ አይቆረጥም በዚያ ላይ እግርኳስ ነው። በዚያ ላይ ስብስቡ ከአምና የተሻለ ጠንካራ ስብስብ አለን በዚህም ደስተኛ ነኝ አምና  ላለመውረድ የሚጫወተው መቻል ዘንድሮ ለዋንጫ መጫወቱ ለውጡን ያሳያል።  እንደ ቡድን አሪፍ ነን ቋሚ ተሰላፊ ለመሆን ጠንካራ ፉክክር ያለበት ክለብ ነው በጉዳት ምክንያት ከቡድኑ ተለይቼ ወደ መስመሩ የገባሁት አሁን ነው  ቦታህን ካስነጠክ  ለመመለስ ከባድ ፈተና የሚገጥምህ ቡድን ነው ያለን … ጥሩ አሰልጣኝ አለን ቡድናችንን በጠንካራ መንገድ እየመራው እዚህ ደርሰናል ለዋንጫ የሚጠበቅ የሚፎካከር ቡድን አድርጎታል።

ሊግ:-  በአንድ ቦታ ተሰባስቦ መጫወት ተመቸህ…?

በረከት:– የሀገሪቷ ሁኔታ ያመጣው ክስተት ነው ከቦታ  ቦታ ተዟዙሮ መጫወት ከቀረ አመታት ተቆጠሩ በርግጥም ደስ የሚል ነገር አለው ውድድሩ አንድ ቦታ መሆኑ ያለው ጥቅም ከስፖርተኛም ይሀን ከስፖርት ቤተሰብ ጋር ያግባባል ትውውቅ ይፈጥራል ከጉዞ ጋር ተያይዞ የሚከሰት ድካም የለም አቋምህን አጠናክሮ ሜዳ ላይ የማሳየት እድል ይፈጥራል። ሜዳዎቹን ስናይ ጥሩ የሚባለው የድሬዳዋ ሜዳ ነው የተሻለ ነገር እንድናሳይ ረድቶናል… ምንም ሰበብ የማታቀርብበት ሜዳ ነው የሀዋሳ ስታዲየም ጥሩ ቢሆንም ዝናብ ከዘነበ የመጨቅየት  ነገር ይታያል ባህርዳር ሰላም ቢሆን ሜዳው ይመች ነበር ግን አልሆነም።

ሊግ:- የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ለሁለተኛ ጊዜ የማንሳት ጉጉት  የለብህም ..?

በረከት:– ኧረ በደንብ ነው ያለብኝ እንጂ… ፋሲል ከነማ እያለን የመጀመሪያውን የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ  አንስተን በቀጣይ አመት ላይ ለመድገም ከፍተኛ ጥረት አድርገን ለማሸነፍም ተቃርበን ቅዱስ ጊዮርጊስ ወስዶታል በመቻል ማሊያ ሁለተኛውን ዋንጫ ለማንሳት  ከፍተኛ ፍላጎት አለብኝ።

ሊግ:- በአንድ ዋንጫ የሚረኩ ተጨዋቾች  አሉ… አንተስ በአንድ ዋንጫ  አልረካህም ..?

በረከት:- ይሄማ ተገቢ አይደለም  እኔንም አይመለከትም ቅዱስ ጊዮርጊስን ተመልከት ….  ቅዱስ ጊዮርጊስ ብዙ የሊግ ዋንጫ ያሸነፈ ቡድን ነው እዚያ ቡድን ውስጥ አራት ኘምስት ጊዜ ዋንጫ ያነሳ አለ  የዋንጫ ጉጉታቸው ግን አሁንም አለ በጣም ይጥራሉ  በአንድ ዋንጫ የሚያበቃ ታሪክና  አቅም እንዲኖረኝ አልፈልግም ደጋግሜ ዋንጫ ማሸነፍ  እፈልጋለሁ።

ሊግ:-  በቀጣይ 27ኛ ሳምንት መርሃጎብር ከቀድሞ ክለብህ ፋሲል ከነማ ጋር ትገናኛላችሁ… ፋሲል ከነማን ስታስብ ምን ስሜት ይፈጥራል..?

ሊግ:-  በቀጣይ 27ኛ ሳምንት መርሃጎብር ከቀድሞ ክለብህ ፋሲል ከነማ ጋር ትገናኛላችሁ… ፋሲል ከነማን ስታስብ ምን ስሜት ይፈጥራል..?

በረከት:-  ፋሲል ከነማ ብዙ ታሪክ የሰራሁበት የሊግ ዋንጫ ያነሳሁበት  ጠንካራ የሆነ ክለብ ነው በጨዋታው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተሸንፈው ስለመጡ ወዳሸናፊነት ለመመለስ እንደሚገቡ ይጠበቃል እኛም ለዋንጫ የምናደርገውን ፉክክር ለማስቀጠል የግድ ሶስቱ ነጥብ ስለሚያስፈልገን ከእግዚአብሄር ጋር ለማሸነፍ እንጥራለን እንደሚሳካም ርግጠኛ ነኝ በአንደኛ ዙር አቻ ነው የተለያየነው በዚህኛው ግን ድሉ የኛ ነው የሚሆነው….

ሊግ:–  ተደጋጋሚ  ጊዜ ነጥብ መጣላችሁ ተፎካካሪነታችሁን አልቀነሰም….?

በረከት:– አዎ የተወሰነ ነገር ቀንሷል። በተለይ ከሻሸመኔ ከተማ ጋር 2 ለ 2  ተለያይተን ሁለት ነጥብ መጣላችን ትልቅ ዋጋ ነው ያስከፈለን…. ግን አሁንም ፉክክር ውስጥ አለን እስከ መጨረሻ  እንታገላለን።

ሊግ:– ተደጋጋሚ ነጥብ መጣላችሁን ግን እንዴት አየኧው..?

በረከት:– ዘንድሮ በተለይ  በተሳሳተ የዳኛ ውሳኔ እየተጎዳን ነው ድሬዳዋ ላይ ነጥብ ጥለን ዋጋ ያስከፈሉን ጨዋታዎች ነበሩ በዚህ አዝነናል  በቀደም  ከሻሸመኔ ከተማ ጋርም ስንጫወት የጣልናቸው ነጥቦች ያበሳጫሉ። በዋንጫ ፉክክር ላይ  ላለ ቡድን የጣልነው ነጥብ ያበሳጫል ስጋትም ይፈጥራል በዚህ  አጋጣሚ ከዳኝነት ጋር ተያይዞ ጥሩ ጥሩ ዳኞች አሉ…. የተሻለ የሚያጫውቱ አቅም ያላቸው  ጥሩ ጥሩ ዳኞቸ አሉ …በተቃራኒው ደግሞ ደካማ ውሳኔያቸው ዋጋ የሚያስከፍሉም አሉ.. የዳኞች ኮሚቴ ሲመድባቸው  ጥንቃቄ ማድረግ  ያለበት ዳኞቹ ብቃት ላይ ነው በተለይ ድሬዳዋ ላይ በዳኛ  ያጣናቸው ነጥቦች ያስቆጫሉ… ኮሚቴው ቢቀጣ ከምደባ ቢያስቀራቸው በተለይ ለዋንጫና ላለመውረድ የሚደረጉ ጨዋታዎች ላይ የተሻሉ የሚባሉ ዳኞች ቢመደቡ ጥሩ ነው ከትችት ያድናልና….

ሊግ:- ፕሪሚየር  ሊጉ ጠንካራ ነው ማለት ይቻላል..?

በረከት:– አዎ ለውጥ አለው … በፊት በፊት ቅዱስ ጊዮርጊስ ብቻ ነው ዋንጫ የሚወስደው አሁን ተቀይሯል ጠንክሮ ለመጣ እድሉ አለው ባለፉት አራት አመታትም ይሄ ነው የታየው…… ከእንድ የዋንጫ አሸናፊ ፉክክር  ወጥተን አሁን ላይ ያሉት  የዋንጫ ተፎካካሪዎች  ክለቦች ቁጥር ጨምሯል ይሄ ደግሞ የተፎካካሪዎቹ አቅም  መጨመሩን ማሳያ ነው አሁንም   እንደኔ የዋንጫ አሸናፊው አዲስ ቡድን መሆኑን አልጠራጠርም።

ሊግ:– ከኢትዮጵያ  ንግድ ባንክ ውጪ  የዋንጫ ተፎካካሪ አለባችሁ ….?

በረከት:– አይመስለኝም … ከላያችን ያለው  ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውጪ  የዋንጫ ተፎካካሪ  ቡድን የለም  ከእኛና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውጪ ሌላ የዋንጫ ተፎካካሪ ቡድን አለ ብዬ አላምንም…. አራት ጨዋታ  እየቀረ የነጥብ ልዩነቱ በመስፋቱ ፉክክሩ የሁለቱ ክለቦች ብቻ እንዲሆን አድርጎታል።

ሊግ:- በእስካሁኑ 26ቱ ጨዋታዎች በመሸነፋችሁም ይሁን  በማሸነፋችሁ  የማትረሳው  ጨዋታ የትኛው ነው…?

በረከት:- ሁሉም ጨዋታ ስትሸነፍ የምታጣው ተመሳሳይ  3 የጥብ ነው  አንዳንዴ ግን የሚያበሳጭ ሽንፈት ይገጥምሃል ድሬዳዋ ላይ በኢትዮጵያ መድን ስንሸነፍ በጣም ተበሳጭቻለሁ አልረሳውም የዳኝነት ክፍተቶች ቢኖሩም አሸንፈን መውጣት  የነበረብን ጨዋታ ባለቀ ሰአት የተቆጠረው ግብና የገጠመን ሽንፈት አበሳጭቶኛል። በተሻለ መንገድ ተፎካካሪ እንዳንሆን ያደረገን ጨዋታ በመሆኑ የምረሳው አይመስለኝም በተቃራኒው  የተደሰትኩበት ጨዋታ  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ያሸነፍንበት ጨዋታ  አሁን ድረስ ያስደስተኛል። አንድ ብጨምር በቅርቡ ደግሞ እንዲሁ ሀዋሳ ከተማን የረታንበት ጨዋታም አይረሱኝም።

ሊግ:– ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን አሸንፋችሁ ጣፋጭ ድል አግኝታችሁ አሁን በ5 ነጥብ መበለጣችሁ አያበሳጭም..?

በረከት:-  በጣም ያበሳጫል… ምክንያታቸው ምንም ይሁን በፊት የጣልናቸው ነጥቦች ዋጋ አስከፍለውናል ብዬ አስባለሁ…ገድለን ማጠናቀቅ የነበረብን  ጨዋታዎችን ነጥብ እየጣልን መምጣታችን ጎድቶናል ያስከፋሉ… እንዲመሩን እድል የሰጣቸው ያ ክፍተት ነው  አሁንም ሊጉን እየመሩ ነው እኛም እድላችን እስኪሟጠጥ የምንችለውን እናደርጋለን።

ሊግ:– አርሰናልን አያስታውስህም .?

በረከት:– /ሳቅ በሳቅ/ አዎ በደንብ ያስታውሰናል እውነት ነው ባለቀ ሰኘት አርሰናልን እየሆንን  ነው /ሳቅ/

ሊግ:- ከሽመልስ በቀለ ጋር  በመጫወትህ ተጠቀምክ…?

በረከት:-  የኢትዮጵያ ሌጀንድ ነው ሲኒየር ነው ከሱ ጋር በመጫወቴ ብዙ ልምድ እንድቀስም አድርጎኛል ክህሎቴን አሳድጌያለሁ ትልቅ ተጨዋች እንደመሆኑ ሲቆጣ የሚለውን ሰምቼ ለመተግበር  ነው የምጥረው በሱ ደስተኛ ነኝ አብሬው በመጫወቴ ኩራት  ይሰማኛል በእሱ ደረጃ ለመድረስ ነው የምጫወተው።

ሊግ:-  ዋሊያዎቹን ማገልገል ላይ ብዙም የለህም .. ለምን ግን …? የውጪ ዕድልስ አልመጣም..?

በረከት:- ለብሄራዊ ቡድን መጫወት የማያልም ተጨዋች የለም …በእግርኳስ  የአሰልጣኝ ምርጫ  ወሳኝ ነው እጠራና ስሄድ ተጠባባቂ ነኝ አምነው  እስኪያስገቡኝ ድረስ የምችለውን እያደረኩ እየጠበኩ ነው በተረፈ አገሬን የማገልገል ፍላጎቴ  ከፍተኛ ነው እንደ ሀገር ጥሩ ጥሩ ተጨዋቾች ይጠራሉ  ከእነሱ ጋር መፎካከር አሰልጣኙን ማሳመን ይጠበቃል እንደኔ ግን ቋሚ ሆኖ የመሰለፍ አቅሙ አለኝ  ብዬ አምናለሁ።  የውጪ ዕድል ላልከው አሁን ላይ የውጪ እድል አልመጣም በቀጣይ ግን  እንደሚመጣ  ተስፋ አደርጋለሁ።

ሊግ:– ቲየሪ ኦነሪ ብለን አርሴን ቬንገር ካልን ቤኪ ብለንስ …?

በረከት:- /ሳቅ/ ቲቲ ብለን አርሴን ካልን በረከት ብሎማ ያለጥርጥር  ዳዊት ታደለና አሸናፊ በቀለ  ብለህ ትጠራለህ….. በዚህ አጋጣሚ ያሰለጠኑኝን አሰልጣኞች በመሉ ማመስገን እፈልጋለሁ።

ሊግ:-  የበረከት  አቋም ጥሩ ነው ወይስ ወደፊት እንጠብቀው…?

በረከት:– ረጅም ጊዜ ተጎድቼ ከሜዳ ርቄ ስለነበር አሁን ያለኝ አቋም እንደ በፊቱ  ባይሆንም ለክፉ የሚሰጥ አይደሀም ወደ ጥሩ አቋሜ እየተመለሴኩ ነው። በነገራችን ላይ ጉዳቴ ከቤተሰቦቼ ጋር ጊዜ እንዲኖረኝ በአዕምሮዬ አርፌ እንድመለስ  አድርገጓል በአንድ ውድድር ዘመን ከቤተሰቤ ጋር ከሶስት ወር በኋላ እንደ መገናኘታችን ናፍቆቱ ይከብደኝ ነበር ያም ሆኖ አምነንበት የመጣውን እየተቀበልን እንገኛለን  በነገራችን ላይ የቤተሰብ ናፍቆቱ ቢኖርም ቻል ማድረግ ይጠበቃል በዚሁ አጋጣሚ ሁሉን ነገር የምትሸፍንልኝ የቤቴን ሃላፊነት የምትቆጣጠረውን  ባለቤቴ  ቤዛዊት ሽመልስን አመሰግናለሁ።  በጣም እንደምወዳትና እንደማመስግናት መግለጽ እፈልጋለሁ።

ሊግ:- በእኛ ሀገር እግርኳስ ባይኖር የምትለው  ምንድነው ..?  ዘና የምትለውስ በምንድነው?

በረከት:– ባይኖሩ ከምላቸው  አንደኛ ከዳኞች ጋር ያሉ ንትርኮች ውዝግቦች ሁለተኛ ደግሞ ተጨዋች ሆነው ሰአት ለመግደል የሚደረገው ጥረት ያበሳጫል።  እንደ ውጪው አይደለም በውጪ ኳስ የባከነ ሰአት ተቆጥሮ ነው የሚጨመረው በእኛ ሀገር ግን ከአራትና አምስት ደቂቃ በላይ ተጨምሮ አያውቅም ሁሉም ተጨዋች ይህን ቢተው ደስ ይለኛል የምትዝናናበት ላልከው  ጊዜ ሲገኝ ቤተሰቦቼና ጓደኞቼ ጋር  ማሳለፍ እፈልጋለሁ ይሄ ያስደስተኛል። በተለይ ጊዜ ሳገኝ ከልጆቼ ጋር ማሳለፍ ያስደስተኛል።

ሊግ:– ጨረስኩ….የመጨረሻ ቃል..?

በረከት:– እስካሁን የረዳኝ  አብሮኝ ላለ ፈጣሪዬ ክብርና ምስጋና ይድረሰው ከዚያ በመቀጠል ቤተሰቦቼን፣ ጓደኞቼን ፣ አሰልጣኞቼን ፣ በኔ ነገር ላይ  አንድም ይሁን ለጨመሩ ሁሉ ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለሁ።

spot_img
የቀደሙ ጽሁፎች..የሊግ ጉዞ ቀጥሏል …
ቀጣይ ጽሁፎች..የሊግ ጉዞ ቀጥሏል …
ተመሳሳይ ጽሁፎች

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this: