ኩባንያችን ላለፉት 130 ዓመታት የቴሌኮም አገልግሎት በመስጠት በሀገራችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት እንዲሁም በዜጎች ኑሮ መሻሻል ላይ የበኩሉን አስተዋጽዖ በማድረግ አጠቃላይ የአስቻይነት ሚናውን በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡ በተለይም ከኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ባሻገር የዲጂታል እና የዲጀታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን በማቅረብ የድርጅቶችን እንዲሁም የግለሰቦችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ለማሳለጥና አካታች እድገትን ለማረጋገጥ ቀዳሚ የመሪነት ሚና ለመጫወት የሚያስችል መሪ (LEAD Growth Strategy) የተሰኘ የሦስት ዓመት የእድገት ስትራቴጂ ቀርጾ ተግባራዊ በማድረግ በስትራቴጂ ዘመኑ ሁለት ተከታታይ ዓመታት የላቀ ውጤት ማስመዝገቡ ይታወሳል፡፡
ኩባንያችን በአዲስ ጅማሮ በአዲስ እይታ የጀመረው አዲሱ የ2017 በጀት አመት የስትራቴጂ ዘመኑ ሶስተኛው አመት ሲሆን በበጀት አመቱ ኩባንያችን በተሰማራበት በሁሉም መስክ መሪነቱን በማስቀጠል በሀገራችን የቴሌኮም ዘርፍ የህዝባችን ማህበረሰባዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁለንተናዊ እድገት ላይ አዎንታዊ አስተዋጽዖ የሚያመጡ፣ የተቋማትን አሰራር ቅልጥፍናና ምርታማነትን የሚያሳድጉ እንዲሁም በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ወሳኝ ሚና ያላቸው ዘርፎች አቅማቸውን አሟጠው እንዲጠቀሙ የሚያስችላቸውን ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በማስታጠቅ የተጀመረውን የሀገራችንን ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የማፋጠን እና ዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታን ማሳለጥን ታሳቢ ያደረገ እቅድ በማዘጋጀት ወደ ስራ ገብቷል፡፡
ሰውን ማዕከል ያደረገ የእድገት እና የቀጣይነት እቅድ
የበጀት ዓመቱ እቅድ ሲዘጋጅ የሦስት ዓመቱ ስትራቴጂ የሁለት ዓመት ትግበራን በመቃኘት የኩባንያችንን ተወዳዳሪነት እና አስተማማኝ እድገት ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ ተቋሙ ላይ ፍላጎትና ተጽዕኖ ሊኖራቸው የሚችሉ የመንግስት የፖሊሲ ሰነዶች፣ የመንግስት የልማትና እድገት እቅዶች (የ10 ዓመት የመንግስት እቅድ እንዲሁም የሀገር በቀል የኢኮኖሚ እድገት እቅድ)፣በቅርቡ የተከናወነው የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ለውጥ፣ የውስጥና የውጭ ባለድርሻ አካላት (የደንበኞች፣ የሠራተኞች፣የተቆጣጣሪ አካላት፣ የቴክኖሎጂ አቅራቢዎችና የተለያዩ የመንግስት አካላት እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት) ፍላጎትና ተጽዕኖ በጥልቀት ተዳሰዋል፡፡
በተጨማሪም በቴሌኮም ዘርፍ የተሰማሩ ሌሎች ተቋማት ያላቸውን የገበያ እንቅስቃሴና ልምድ፣የቴሌኮም ኢንዱስትሪ እድገት ዋና ዋና አዝማሚያዎችና የዓለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎችን በመተንተን፣ እንዲሁም የኩባንያችን ውስጣዊ ጥንካሬና ውስንነቶችን በመለየት፣ውጫዊ መልካም አጋጣሚዎችና ስጋቶችን በመተንተን የተቋሙን ተጨባጭ አቅምን በመለየት ለእድገት እና ለቀጣይነት የሚያበቃውን ተግባራት በመቃኘት የተዘጋጀ እቅድ ነው፡፡
ኩባንያችን ስትራቴጂያዊ የትኩረት መስኮቹን ማለትም ምርጥ የደንበኛ ተሞክሮን ማረጋገጥ፣ ቀጣይነት ያለው የቢዝነስ እድገት፣ የቴክኖሎጂ ልህቀት ማረጋገጥ፣ ሰው ተኮርና ከፍተኛ አፈጻጸም ያለው ተቋም መገንባት፣የኦፕሬሽን ልህቀት እና ቀዳሚ ተቋማዊ ገጽታ ግንባታ ሥራዎች ያለውን የሰው ኃይል፣ እውቀትና ሀብት በአግባቡ በመምራት በደንበኞቹ፣ በአጋሮቹና በባለድርሻ አካላት ተመራጭ ኩባንያ ለመሆን በትጋት የሚሰራ ሲሆን፣ ቀጣይነት ያለው እድገት ለማረጋገጥ እና ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን ምላሽ ለመስጠት (to address strategic issues) ለኮርፖሬት ስትራቴጂያዊ ግቦች ተገቢውን መለኪያና ዒላማ በማዘጋጀት ከሐምሌ 1 ቀን 2016 ጀምሮ ወደ የሥራ ክፍሎች ካስኬድ (cascade) በማድረግ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡
ስትራቴጂው በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ የመጣውን የደንበኛ ፍላጎትን ለማርካት፣ የቴሌኮም ስርጸትን በማሳደግ የዲጂታል ኢኮኖሚን ለመደገፍና አጠቃላይ የሀገሪቱን ምርታማነት ለማሳደግ እንዲሁም የተቋሙን የገቢ ምንጭ ከመደበኛ የቴሌኮም አገልግሎቶች ወደ ዳታና የይዘት አገልግሎቶች፣ የክላውድ፣ የኢንፍራስትራክቸር እና የኢንተርፕራይዝ ሶልዩሽንስ ትኩረት በማድረግ፣ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ላይ አዳዲስ አገልግሎቶችን በመጨመር እና በማስጀመር እንዲሁም አዳዲስ አገልግሎቶችና የቢዝነስ ዘርፎች ለመቀላቀል ዝግጅት በማድረግና ያሉትን መልካም ተሞክሮዎች በማጠናከር የተቋሙን ቀጣይነት፣ እድገትና ትርፋማነትን ለማሳደግና አስተማማኝ ለማድረግ ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡
የበጀት ዓመቱ ዋና ዋና እቅዶች አስቻይ የቴሌኮም እና የዲጂታል መሰረተ ልማት እና የሲስተም መደላድሎች
ኩባንያችን በበጀት አመቱ መሪ የዲጂታል አገልግሎት አቅራቢ (A Leading Digital Solutions Provider) የመሆን ራዕዩን እያሳካለመቀጠል እና የሀገራችንን ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን በማፋጠን አለም ከደረሰበት የእድገት ደረጃ በማድረስ ተወዳዳሪ ለማድረግ ቀድሞ የተዘረጉ የቴሌኮም እና የዲጂታል መሰረተ ልማቶችን አሟጦ በመጠቀም እንዲሁም በከፍተኛ ሁኔታ በማደግ ላይ የሚገኘውን የደንበኛን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ የደንበኛ እርካታን የሚያሳድጉና ተሞክሮን የሚያሻሽሉ ጥራት ያለው አገልግሎቶች ለማቅረብ የሚያስችሉ ተጨማሪ የቴሌኮም እና የዲጂታል መሰረተ ልማቶችን በመዘርጋት፣ ዜጎች፣ ቢዝነሶች እንዲሁም ተቋማት ያለመከልከል አቅማቸውን እንዲጠቀሙ የሚያስችሏቸውን ልዩ ልዩ ዘመናዊ ዲጂታል መፍትሔዎች ማቅረቡን የሚቀጥል ይሆናል፡፡
ለዚህም የቴሌኮም ኔትዎርክ ማስፋፋፊያና የአገልግሎት ጥራት ማስጠበቂያ ስራዎችን አጠናክረን የምናስቀጥል ሲሆን አዳዲስና ዘመናዊ የቴሌኮም እና የዲጂታል መሰረተ ልማቶችን እና ሲስተሞችን ማስፋፊያና ማጠናከሪያ ፕሮጀክቶችን በመተግበር የተጀመሩትን ሀገራዊ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ተግባራት አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
የቴሌኮም መሰረተ ልማትን ለማስፋፋት የተያዙ እቅዶች
- የቴሌኮም ሽፋንን በመጨመር የቴሌኮም ስርጸት መጠንን የሚያሳድጉ 1,298 አዲስ የሞባይል ጣቢያዎችን ለመገንባት፤
- 500 ተጨማሪ ከተሞችን የ4ጂ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ፤
- 15 ተጨማሪ ከተሞችን የ5ጂ አገልግሎት ተጠቃሚለማድረግ፤
- በገጠራማ አካባቢዎች የአገልግሎት ተደራሽነትን በማሳደግ በገጠር እና በከተሞች መካከል ያለውን የዲጂታል ክፍተት (digital divide) ለማጥበብ በገጠር 331 የሩራልኮኔክቲቪ ቲሶሉሽኖችን እንዲሁም 165 የሞባይል ኔትወርክ ጣቢያዎችን በመገንባት በድምሩ 496 ጣቢያዎች በማድረስ ለ1000 የገጠር ቀበሌዎች የኔትወርክ ሽፋን ለመስጠት ታቅዷል።
- 320 ሺህ አዳዲስ ኦ.ዲ.ኤን በመገንባት ተጨማሪ ደንበኛ ለማስተናገድ የሚያስችል የፊክስድ ኔትዎርክ አቅምን ለማሳደግ፣ 1,553 ኪ.ሜ የሜትሮ ማስፋፊያ ለመስራት፣ የፋይበር ኔትዎርክን ከ21.8 ሺህ ኪሜ ወደ 22 ሺህ 200 ኪ.ሜ ለማሳደግ እንዲሁም International Gateway (IGW) አቅምን በ25% ለማሳደግ ታቅዷል፡፡
ዲጂታል መሰረተ ልማትን ለማስፋፋት የተያዙ እቅዶች
- ከመሰረታዊ የቴሌኮም አገልግሎቶች ባሻገር የድርጅት ደንበኞችን አሰራር ስርዓት የሚያዘምኑ እና የቢዝነስ እንቅስቃሴ የሚያሳልጡ እንዲሁም ተቋማችንን ልዩ የሚያደርጉ የዲጂታል መፍትሄዎችን እንደክላውድ እና ኤጅ ኮምፒውቲንግ (cloud and edge computing)፣ አይኦቲ (IoT) የመረጃ ማዕከል አገልገሎት (Data center)፣ የጥሪ ማዕከል አገልግሎት (CcaaS)፣ የቪዲዮ፣ የጌም እና የሙዚቃ አገልግሎቶች፣ የዲጂታል ግብርና፣ ጤና፣ ትምህርት፣ ስማርት ከተማ የመሳሰሉትን አቅርቦት ለማሳደግና ለማስፋት፤
- የዳታ ሴንተር IT load capacity በ2.8 MW ማሳደግ፤ የክላውድ አገልግሎቶችን ከማሳደግ አንፃር Cloud computing አዲስ 22,272 vCPU በመጨመር ማሳደግ፤ Enterprise storage አዲስ 1.49PB በመጨመር ማሳደግ፣ Objective Storage 4.5 PB እና የEdge cloud ማስፋፊያ ለማከናወን፤
- የIT ሲስተም ከማዘመንና ከማሳደግ አንፃር Cloud Business Solutions (CBS) እና Customer Relationship Management (CRM) ደንበኛ የማስተናገድ አቅም ከ80 ሚሊዮን ወደ 90 ሚሊዮን ማሳደግ፤
- የAI ትግበራን ከማሳደግ አንፃር የተጀመሩትን አጠናክሮ መቀጠል እና በኔትዎርክ ፐርፎርማንስ፣ የቴሌኮም ማጭበርበርን መከላከልና መለየት እንዲሁም የደንበኞችን አገልግሎት ከማሻሻል አንፃር በስፋት ጥቅም ላይ ለማዋል ታቅዷል፡፡
በበጀት አመቱ የታቀዱ ምርት እና አገልግሎቶች
ከላይ የተጠቀሱትን የቴሌኮም እና የዲጂታል መሰረተ ልማት ማስፋፊያዎችን በማድረግ በበጀት አመቱ የደንበኞችን አጠቃቀም የሚያሳድጉ አዳዲስ ምርት እና አገልግሎቶችን የማቅረብ እንዲሁም ነባር ምርት እና አገልግሎቶችን በደንበኞች ፍላጎት መሰረት የማሻሻል፤ የኢንተርፕራይዝ ደንበኞችን ፍላጎት የሚመልሱ ተጨማሪ አገልግሎቶችን የማቅረብ እቅድ የተያዘ ሲሆን
- በዚህም 257 አዳዲስና የተሻሻሉ የግለሰብ ደንበኛና ለኢንተር ፕራይዝ ደንበኞች የሚሆኑ ምርትና አገልግሎቶችን ለገበያ ለማቅረብ ታቅዷል፡፡
የቴሌብር ተደራሽነትን እና የዲጂታል ፋይናንስ አካታችነትን ለማሳደግ የተያዙ እቅዶች
የሀገራችንን የዲጂታል ፋይናንስ አካታችነትን በማሳደግ ረገድ የላቀ ሚና እየተጫወተ ያለውን የቴሌብር አገልግሎት በስፋት ተደራሽ ለማድረግ የቴሌ ብር ወኪሎችን ቁጥር በ28% በማሳደግ 275 ሺህ ለማድረስ እንዲሁም በቴሌ ብር ግብይት የሚፈጽሙ ነጋዴዎችን (Merchant) ቁጥር በ102% በማሳደግ 367 ሺህ ለማድረስ እና የቴሌብር ደንበኞችን ቁጥር በ15.7% በመጨመር 55 ሚሊዮን ለማድረስ ታቅዷል፡፡
የደንበኞችን ፍላጎት የሚያሟሉና እሴት የሚጨምሩ የቴሌብር ምርቶችንና አገልግሎቶችን በማቅረብ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን፣ የሀገር ውስጥ የዲጂታል ገንዘብ ዝውውርን፣ የኤሌክትሮኒክ ንግድ ክፍያዎችን፣ አለም አቀፍ የኦንላይን ክፍያዎችን፣ ተጨማሪ አጋሮችን በማሳተፍ የሃዋላ አገልግሎቶችን ለማሳደግ ታቅዷል፡፡
የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግ የተያዙ እቅዶች
ኩባንያችን የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግ ዓለም አቀፍ ስትራቴጂያዊ አጋርነትን በማስፋት እና ተወዳዳሪ አገልግሎት በማቅረብ ዓለም አቀፍ ገቢንና የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ የአገልግሎት ዘርፎችን በመጠንና በአይነት በማሳደግ በተለይም የዓለም አቀፍ አገልግሎትና የረሚታንስ (የሀዋላ) አገልግሎትን በማሻሻልና አጋሮችን በማስፋት በበጀት ዓመቱ የውጭ ምንዛሪግኝት መጠን ወደ 282.85 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለማሳደግ ታቅዷል፡፡
ወጪን ለመቆጠብ የተያዙ እቅዶች
ባለፉት ሶስት አመታት የተፈጠረውን ወጪ ቆጣቢ ባህል በማስቀጠል የሃብት እና እሴት አስተዳደርን ማሳደግ፣ የሀብት አጠቃቀ ምን ማሳደግ፣ የግዥ ሂደትን በማዘመን ወጪዎችን መቀነስ፤በበጀት ዓመቱ የገቢ አማራጮችንና የገቢ መጠን ከማሳደግ በተጨማሪ የኩባንያው የወጭ ቁጠባ (DO2SAVE) ስትራቴጂ ትግበራን አጠናክሮ በመቀጠል ብር 3.2 ቢሊዮን ያህል ወጭን ለመቆጠብ (Cost Optimization) የታቀደ ሲሆን ይህም የኩባንያውን ትርፋማነትና ቀጣይነት ያለው እድገት ለማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ይኖረዋል፡፡
የሰው ኃይል እና ተቋማዊ አቅም ለመገንባት የተያዙ እቅዶች
- የኩባንያችን አመራር ለፈተና የማይበገር (Resilience) በቢዝነስ ከባቢው ከሚፈጠሩ ሁኔታዎች ጋር በቀላሉ በመላመድ (Adaptive) ተግዳሮቶችን ወደ እድል የመቀየር ሂደቱን አጠናክሮ ማስቀጠል፤ የሰራተኞችን ወቅታዊ የክህሎት ስብጥር በመገምገም የክህሎት ክፍተት ትንተና በማካሄድ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ለመደገፍ የሚያስፈልጉትን ዲጂታል ክህሎት እና ብቃቶች በመለየት የሳይበር ደህንነትን፣ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ የመረጃ ትንተና እና ቀልጣፋ እድገትን ጨምሮ የተለያዩ ዲጂታ ልብቃቶችን የሚዳስስ አጠቃላይ የዲጂታል ክህሎት ስልጠና መስጠት።
ከማህበራዊ ኃላፊነት (CSR) እና ዘላቂ ልማት አንጻር የተያዙ እቅዶች
ኩባንያችን ከሚሰጠው የቴሌኮም አገልግሎት በተጨማሪ ለማህበረሰቡ ፋይዳያላቸው የማህበራዊ ኃላፊነት (CSR) ጉዳዮች ላይ ጉልህ ሚና እንደሚጫወት የሚታወቅ ሲሆን፣ በዚህ በጀት ዓመትም በጤና፣ በትምህርት፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በሰብዓዊ እርዳታና መሰል የበጎ አድራጎት ሥራዎች እንዲሁም ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ በመሳተፍ ማህበራዊ ኃላፊነቱን መወጣቱን አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
የ2017 በጀት ዓመት ዒላማዎች
ከላይ የተጠቀሱትን ዝርዝር እቅዶች በማሳካት በ2017 በጀት ዓመት አጠቃላይ የደንበኞችን ብዛት በ6% በመጨመር 83 ሚሊዮን ለማድረስ የታቀደ ሲሆን የሞባይል ደንበኞችን በ5.5% በመጨመር 79.7 ሚሊዮን ማድረስ፣ የሞባይል ዳታና ኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን በ16% በመጨመር 47.4 ሚሊዮን ማድረስ እንዲሁም የፊክስድ ብሮድባንድ ደንበኞችን በ25% በመጨመር 934 ሺህ በማድረስ አጠቃላይ የቴሌኮም ስርጸት መጠንን 73% ለማድረስ ታቅዷል፡፡
ገቢን ከማሳደግ አኳያ ከመደበኛ የቴሌኮም ገቢ ምንጮች በተጨማሪ ሌሎች እሴት የሚጨምሩ አገልግሎቶችን በመጨመር፣ ዲጅታል፣ አዳዲስ እና የተሻሻሉ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ አገልግሎቶችን ለገበያ በማቅረብ፣ የኢንተርፕራይዝ ሶሉሽንስ፣ የቴሌብር ተደራሽነትና የአገልግሎት አይነቶች እንዲሁም አጋሮችን በማሳደግ፣ የአገልግሎት አሰጣጡን በማሻሻል እና የደንበኛ እርካታን፣ ቆይታንና ታማኝነትን በማሳደግ በ2016 በጀት ዓመት የተገኘውን 93 ቢሊየን ብር ገቢ በ74.7% በማሳደግ 163.7 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ታቅዷል፡፡
በመጨረሻም ኩባንያችን ባለፈው በጀት ዓመት ላስመዘገበው የላቀ ውጤት አስተዋጽኦ ላደረጋችሁ ደንበኞቻችን፣ የኩባንያችን የስራ አጋሮች፤ የምርትና አገልግሎቶቻችን አከፋፋይ ወኪሎች፣ አቅራቢዎች፣ ቬንደሮች፣ የሚዲያ አጋሮቻችን እንዲሁም ባለድርሻ አካላት በሙሉ ልባዊ ምስጋናችን ይድረሳችሁ እያልን፣ በዚህኛው በጀት አመትም የሀገራችንን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እውን ለማድረግ ከኩባንያችን ጋር አብራችሁ እንድትሰሩ ጥሪያችንን በአክብሮት እናቀርባለን፡፡